ለሀገር ዕድገት ማነቆ የሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና ሌብነትን ሁሉም ዜጋ ሊታገለው ይገባል- ምሁራን

124

ሆሳዕና:ሰኔ 12/2014 (ኢዜአ)መንግሥት ለሀገር ዕድገት ማነቆ የሆኑት የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና ሌብነትን ለማስወገድ እያደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ጥረት ስኬት ሁሉም ዜጋ በተቀናጀ መንገድና በቁርጠኝነት ማገዝ እንደሚገባው የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ምሁራን አስገዘነቡ።

ምሁራኑ ለኢዜአ እንደገለጹት የመልካም አስተዳደር እጦትና የሌብነት መበራከት በዜጎች ላይ ከብርሃን ይልቅ ጨለማ ከተስፋ ይልቅ ውድቀት እንዲሰማቸው በማድረግ ለለውጥ ማነቆ መሆኑን በመገንዘብ በጋራ ትግል ማክሸፍ ይገባል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን ለፓርላማ አባላት የሰጡት ማብራሪያ መከታተላቸውን ገልጸው፤ ሁሉም ዜጋ ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት ትግል ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ትምህርት ክፍል መምህር ሙሉአለም ኃይለማርያም በሰጡት አስተያየት የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ሌብነት መበራከት የሚሰራውን ሳይሆን ለማይሰራው የመጠቀም ዕድል መፍጠራቸውን አመልክተዋል።

ችግሮቹ በልማት ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ጭምር ከሀገር ባህልና ወግእንዲወጣ በማድረግ ለከፋ ችግር እንዲዳረግ እያደረጉ ነው ብለዋል።

እሳቸው እንዳሉት አሁን ላይ በኢትዮጵያ በአብዛኛው ክፍሎች በተለይ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አካባቢ ሌብነት የተፈቀደ አሰራር እስከ መምሰል መድረሱን በተለያየ መልኩ እየታዘቡ ነው።

የልማትና የዕድገት ፀር የሆኑ ተግባራትን ከስረ መሰረቱ ማስወገድ ለምናልመው ዕድገት ወሳኝ አማራጭ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

መምህር ሙሉዓለም እንዳሉት በሀገሪቱ እየተመዘገበ ያለውን ለውጥ ለማስቀጠል ከመንግስት ጋር ተባብሮ መስራትና የልማት ጸር የሆኑ ድርጊቶች በቁርጠኝነት መታገል ይጠይቃል።

ሌብነትን መቃወም ከአስተሳሰብ ይጀምራል ያሉት መምህሩ የመንግስት ሰራተኞችና አመራሮች ፍትሃዊ የአገልግሎት አሰጣጥን ተደራሽነትን በማጎልበት ህዝብ የተጠማውን የመልካም አስተዳደር አሰራርን በማስፈን የሀገሪቱን እድገት ማስቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ከግብ ለማድረስ የዜጎች ትብብር ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት በዩኒቨርሲቲው የሰላም ትምህርት ክፍል አስተባባሪና የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት መምህር እንዳለ ሙላቱ ገልጸዋል።

ሁሉም ዜጋ ሌብነትና ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች ሲያጋጥሙት ለህግ አጋልጦ መስጠት ሁሉም ሊያደርገው የሚገባ መሆኑን አስገንዝበዋል።

እያንዳንዱ ዜጋ በመልካም አስተዳደር ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመታገል የሀገርን ሀብት ለልማት እንዲውል በማድረግ የድርሻውን  እንዲወጣ አሳስበዋል።

ሰላምና ልማት የተቆራኙ መሆናቸውን መምህር እንዳለ ገልጸው፤ የመልካም አስተዳደር እጦትና የሌብነት መበራከት ለሰላም መደፍረስ፣ ለልማት መደናቀፍ ችግሮች እንደሚዳርጉም ገልጸዋል።

በመሆኑም በመልካም አስተዳደር ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ተወግደው ዜጎች ፍትሀዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ሁሉም በቁርጠኝነት እንዲታገል አሳስበዋል።

ትናንት የተዘራብን ዛሬ እንደበቀለ ሁሉ ዛሬ የምንዘራውና የምንሰራው ለነገ ወሳኝ በመሆኑ ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ ለመፍጠር በልጆች ላይ አበክሮ መስራት እንደሚገባ መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም