በመዲናዋ የክረምቱን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በትኩረት እየተሰራ ነው

115

ሰኔ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የክረምቱን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ከወዲሁ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡

አስተዳደሩ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው በአዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰና የሕይወት ስጋት እንዲሁም የንብረት መጥፋት ምክንያት እየሆነ የመጣውን የክረምት ጎርፍ አደጋ ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

በዚህ መሰረትም የበለጠ አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ የተባሉ ቦታዎችን በመለየት የጎርፍ አደጋ መከላከል ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደ ተግባር በመግባት በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡

May be an image of outdoors

በከተማው ለጎርፍ ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉ ቦታዎችን በዝርዝር በመለየት የተለያዩ የቅድመ መከላከል ስራዎች መከናወናቸውንም ታውቋል::

ለጎርፍ ተጋላጭ ተብለው ለተለዩ ቦታዎች የአጭር እና የረጅም ጊዜ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ወደ ተግባር መገባቱን የገለጸው አስተዳደሩ ህብረተሰቡም በክረምቱ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የተለየ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በተጨማሪም ነዋሪዎች ከተማ አስተዳደሩ እንደየአካባቢዎቹ ተጨባጭ ሁኔታ አስፈላጊ ነው ብሎ የሚያምንባቸውን የመፍትሄ አቅጣጫዎች ሲተገብር ተባባሪ በመሆን ሊያጋጥሙ የሚችሉ አደጋዎችን በጋራ እንዲከላከሉ ማሳሰቡን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡