የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ቀድሞው ሰላማዊ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ መመለሳቸውን ገለጹ

84

ጋምቤላ፣ ሰኔ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች በከተማው ሰላም በመስፈኑ ወደ ቀድሞው ሰላማዊ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ መመለሳቸውን ገለጹ።

የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤትም ከተማዋ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሷን አረጋግጠዋል።

የጋምቤላ ከተማ ነዋሪው አቶ ድሪባ ሌንጮ በሰጡት አስተያየት የጋምቤላ ከተማ በሰላማዊነቷ እንደምትታወቅ ጠቅሰው፤ አሸባሪው ሸኔና ሌሎች ፀረ-ሰላም ቡድኖች ሰሞኑን ሰላሟን ለማደፍረስ ሙከራ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ቡድኖቹ ያሰቡት የሽብር ድርጊት በፀጥታ ኃይሎች ከሽፎ ከተማዋ ወደ ቀድሞ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ መመለሷን ገልጸው፤ ነዋሪው የተለመደ ሰላማዊ ተግባሩን ማከናወን መጀመሩን ተናግረዋል።

የከተማዋን ሰላም ለማደፍረስ ሙከራ ያደረጉት ጸረ ሰላም ሃይሎች በአሁኑ ወቅት የውሸት ወሬ እያሰራጩ እንደሆነም ጠቁመዋል።

"ሕዝባችን በአሁኑ ሰዓት የተረጋጋና በሰላም አብሮ እየኖረ ያለ ሲሆን፤ ሰላማችንም በተስተካከለ መልኩ ተረጋግቶ ይገኛል" ብለዋል።

የጋምቤላ ከተማ ሰሞኑን ያልታሰበ የፀጥታ ችግር አጋጥሟት የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የተረጋጋ ሰላም መኖሩን ሌላው የከተማ ነዋሪ አቶ ዲው የች ተናግረው፤ የከተማዋን ሰላም የማደፍረስ ሙከራ መክሸፉን ገልጸዋል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ደነቀው አቤ በሰጡት አስተያየት በከተማዋ የተረጋጋ ሰላም በመኖሩ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት በበኩሉ የጋምቤላ ከተማ ወደ ቀደመ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሰች መሆኑን አረጋግጧል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ኡገቱ አዲንግ እንደገለጹት፤ ከአራት ቀን በፊት አሸባሪው ሸኔና እራሱን ጋነግ ብሎ የሚጠራው የሽብር ቡድን በጋምቤላ ከተማ በከፍቱት ድንገተኛ ጥቃት የከተማዋ ሰላም ታውኮ ነበር።

የክልሉና የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች የሽብር ቡድኖቹን በመደምሰሳቸው የከተማዋን ሰላም መመለሳቸውን ተናግረዋል።

ሰላም በመስፈኑም በከተማዋ የሚገኙ የንግድ ድርጅቶችም ሆነ የፋይናንስ ተቋማት መደበኛ ስራቸውን ማከናወን መጀመራውን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኖቹ በከተማዋ ጥቃት ከመፈጸሙ ጋር ተያይዞ በበራሪ ጥይት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ሆን ተብሎ በአንድ ብሄረሰብ ላይ የተፈጸመ በማስመሰል በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው ወሬም መሰረተ-ቢስ መሆኑን ገልጸዋል።

አሸባሪው ሸኔና እራሱን ጋነግ ብሎ የሚጠራው የሽብር ቡድን ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም በጋምቤላ ከተማ ሰረገው በመግባት ድንገተኛ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ በክልሉና በፈዴራል የፀጥታ ኃይሎች መደምሰሳቸውን ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም