የህግ ማስከበር ስራው በተለያየ መልኩ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እያደረገ ነው -ዶክተር ድረስ ሳህሉ

138

ባህር ዳር፤ ሰኔ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ያለው የህግ ማስከበር ስራው በተለያየ መልኩ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እያደረገ መሆኑን የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ አስታወቁ።

በዘመቻው በከተማው በህገወጥ መንገድ የተገነቡ ከ3 ሺህ 300 በላይ ቤቶችና ኮንቴነሮች መወገዳቸውና ወንጀል የተጠረጠሩ ከ80 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑ ተመላክቷል

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳስታወቁት በከተማው እየተወሰደ ያለው የህግ ማስከበር ስራ በተለያየ መልኩ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ አስችሏል።

ቀደም ሲል መንግስት ነገሮችን በሆደ ሰፊነት ቢመለክትም በከተማው ስርዓት አልበኝነት እየነገሰ ህገ ወጥ የጦር የመሳሪያ ዝውውር፣ የጥይት ተኩስ ፣ዝርፊያና ስርቆት መስፋፋቱን ገልፀዋል።

"በዚህም ከህብረተሰቡ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ተደጋጋሚ ቅሬታና አቤቱታ ቀርቧል" ብለዋል።

ለህዝብ አቤቱታ ምላሽ ለመስጠት የህግ ማስከበር ዘመቻው ከመጀመሩ ከአንድ ወር በፊት በከተማ አስተዳደሩ የፀጥታ ኮሚቴ በማስወሰን ወደ እርምጃ መግባቱን ጠቁመዋል።

በዚህም በከተማው በዘንዘልማ አካባቢ ተደራጅተው ለሚጠባበቁ ማህበራት በከለለ ቦታ ላይ በህገ ወጥ መንገድ የተገነቡ ከ2ሺ 10 በላይ መኖሪያ ቤቶች እንዲፈርሱ መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

አካባቢውን ከህገ ወጦች ማጽዳት በመቻሉ አሁን ላይ በቦታው የብሎክ ልየታ የተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ በህጋዊ መንገድ ተደራጅተው ለበርካታ ዓመታት ለሚጠባበቁ ማህበራት ለማስተላለፍ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አክለው ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በስራ እድል ፈጠራ መመሪያ መሰረት ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት ብቻ ጥቅም ሰጥተውና ሃብት ፈጥረው ለሌሎች መሸጋገር ሲገባቸው ሳይሸጋገሩ በህገወጥ መንገድ ተይዘው የቆዩ  1ሺህ 291 ኮንቴነሮች መወገዳቸውን ተናግረዋል።

አብዛኛው ኮንቴነሮች በአስፓልት መንገድ ዳር በመሰራታቸው የእግረኛ መንገድን በማጣበብ፣ የህብረተሰቡን እንቅስቃሴ በመገደብ፣ የከተማውን ውበትና ገጽታ በማበላሸት ችግር ፈጥረው መቆየታቸውን አውስተዋል።

በቀጣይም የከተማውን የእድገት ደረጃ ለመጠበቅ ሲባል በአስፓልት ዳር ኮንቴነር የማይሰጥ መሆኑን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል።

''በወሰድነው የህግ ማስከበር ተግባርም ከህገ ወጥ ግለሰቦች ውጭ ያለው የከተማው ነዋሪ ከጎናችን ሆኖ ሙሉ ድጋፉን ሰጥቶናል''ያሉት ዶክተር ድረስ "አሁን ላይ በከተማው ህገ ወጥነት እየከሰመ በመምጣቱ ነዋሪ የሰላም አየር መተንፈስ ጀምሯል" ብለዋል።

"ህገ ወጥ ኮንቴነሮችን በማፍረስ ሂደት ውስጥ በተለያየ ችግር ምክንያት የተዘለሉ በመኖራቸው በቀጣይ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ እርምጃው ተጠናክሮ ይቀጥላል" ሲሉም አክለዋል።

በህግ ማስከበር ዘመቻው እየተወሰዱ ባሉ እርምጃዎች ከህብረተሰቡ መልካም ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።   

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አክለው በህግ ማስከበር ዘመቻው ከዚህ ቀደም ወንጀል ሰርተው የተፈረደባቸው፣ በዝርፊያ፣ ግድያና በሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ ከ80 በላይ ግለሰቦች በቁጥጠር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየተጣራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በተወሰደው ሁሉን አቀፍ ህግ የማስከበር ዘመቻ በተለያየ መልኩ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ከማስቻል በላይ አሁን ላይ ከተማውን የተረጋጋና ሰለማዊ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የህግ ማስከበር ስራውን አጠናክሮ በማስቀጠል በየጊዜው በህብረተሰቡ ዘንድ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያደረገውን ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም