በጉጂ ዞን ከ31 ሺህ በላይ ህጻናት በምገባ ፕሮግራም መደበኛ ትምህርት እየተከታተሉ ነው

111

ነገሌ ፣ሰኔ 11/ 2014 /ኢዜአ/ በጉጂ ዞን ከ31 ሺህ በላይ ህጻናት በምገባ ፕሮግራም መደበኛ ትምህርት እየተከታተሉ መሆኑን የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የምገባ ፕሮግራሙ ዘንድሮ በጉጂ ዞን በነበረው ድርቅ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሳያቋርጡ እንዲከታተሉ እገዛ ማድረጉም ተመልክቷል።

በጽህፈት ቤቱ የትምህርት ስራ ማሻሻያ ባለሙያ አቶ  ሀቢብ ቱና የህፃናቱ ወላጆች በድርቅና በአቅም ማነስ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚተዳደሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ህጻናቱ መደበኛ ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ከኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ለምገባ ፕሮግራሙ 21 ሚሊዮን ብር መመደቡን ገልጸዋል።

በዞኑ ሊበን፣ ጉሚኤልደሎና ጎሮዶላ ወረዳዎች የምገባ ፕሮግራሙ እየተካሄደ ያለው በ98 አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሆኑን  ጠቁመዋል።

ህጻናቱም በዚህ ዓመት የሚሰጣቸውን መደበኛ ትምህርት በመከታተል ላይ ያሉት ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል እንደሆነ ገልጸዋል።

በወረዳዎቹ በምገባ ፕሮግራሙ መደበኛ ትምህርት እየተከታተሉ ካሉት  ህጻናት መካከል 13 ሺህ 99ኙ ሴቶች መሆናቸው ተናግረዋል።

በጉጂ ዞን ዘንድሮ እነዚህን ጨምሮ 475 ሺህ 454 ተማሪዎች መደበኛ ትምህርት በመከታተል ላይ እንደሆኑ ከባለሙያው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።

በዞኑ ሊበን ወረዳ የድቤ አዳማ ትምህርት ቤት መምህርና የፕሮግራሙ ተቆጣጣሪ መምህር እንዳለ ለገሰ ፕሮግራሙ ህጻናቱ ትምህርት እንዳያቋርጡ እገዛ ማድረጉን ገልጸዋል።

በሚከታተሏቸውና በሚቆጣጠሯቸው 54 ትምህርት ቤቶች ብቻ 1ሺህ 400 ተማሪዎች የፕሮግራሙ ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በትምህርት ቤቶቹ ፕሮግራሙ ባይኖር ዘንድሮ ድርቅ ባስከተለው ጫና ከ500 እስከ 600 ህጻናት መደበኛ ትምህርት ያቋርጡ እንደነበር ተናግረዋል።

ህጻናቱ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የክልሉ መንግሥት በራስ አቅም ላደረገው የምገባ ፕሮግራም ድጋፍና ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።

በዚሁ ወረዳ የዱንጎ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሁሴን ኑራ ፕሮግራሙ ተማሪዎች ዓመቱን ሙሉ በምግብ ሳይቸገሩ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አስችሏል ብለዋል።

በጉጂ ዞን በተከሰተው ድርቅ በርካታ ህዝብ ለምግብ እህል እጥረት መዳረጉንና በቤት እንስሳት ላይም ጉዳት መድረሱን  ተናግረዋል፡፡