የምድረ ቀደምቷ የደን ልብስ እና የደን ደናኞቿ ቅኝት

399

የምድረ ቀደምቷ የደን ልብስ እና የደን ደናኞቿ ቅኝት

የምድረ ቀደምቷ

የደን ልብስ እና የደን ደናኞቿ ቅኝት

  • የዛፍ ምስጢሩ ውበቱ ብቻ ሳይሆን፣ ተስፋን ማጫሩ ሕይወትን ማደሱ በመሆኑ ዕጽዋት ማብቀል ዛሬን-አለፍ፣ ትውልድ-ጠቀስ ቁም ነገር ነው።
  • የደን ልማት ዘላቂ ስራ መሆን አለበት፤ ባለቤትነት እንዲጨምርም በወል መሬት ብቻ ሳይሆን በግል ይዞታም አረንጓዴ አሻራ ማንበር ያሻል።
  • የቀጣናውና የታችኛው ተፋሰስ አገራት ከኢትዮጵያ ጎን ሆነው አረንዴ አሻራቸውን በማንበር ለጋራ ጥቅም ዘብ መቆም ይገባቸዋል።

ቅድመ ነገር

የኢትጵያ ሐመልማላዊ /አረንጓዴ/ የገላዋ ገጽታ 60 በመቶ ደናማ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። ኢትዮጵያዊያን ከሺ ዐመታት በፊትም ዛፍ የመትከል ልማድ እንደነበራቸውም እንዲሁ። በደን ላይ የጻፉ ምሁራን ይጠቅሳሉ። የመካከለኛው ዘመን ታሪክ  የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት አፄ ዳዊት (ከ1375-1404) የደን ጭፍጨፋና የእንሳትን አደን ለመከላከል በአገሪቱ ሰባት የአካባቢ ጥበቃ ጣቢያዎች አቋቁመው እንደነበር ዜና መዋዕላቸው ይናገራል። ልጃቸው አጼ ዘርዓ ያዕቆብም የደን ክምችት ጥበቃን አጠናክረዋል፤ ‘የንጉሥ የደን ክልል’ አሰኝተው ኢትዮጵያን የደን ካባ ለማልበስ ጥረዋል። አጼ ልብነ ድንግል ደግሞ ችግኞችን አፍልቶ የመትከል ስራ ስለመጀመራቸው ይወሳል። በርግጥ በመካከለኛው ዘመን ደን የመንከባከብና ዛፍ የመትከል ጅማሮ በዘመነ መሳፍንት እንደተዳከመ ይነገራል።

ሌላው በደን ድነና ታሪካቸው የሚነሳው ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ናቸው። የአጼ ዘርዓ ያዕቆብን ‘የንጉሥ ደን ጥብቅ ስፍራ’ ጽንሰ ሃሳብን አጠናክረዋል። በዘመናቸው ያጋጠማቸውን ፈተናም ለደን ድነና ተጨማሪ ሃይል የገፋፋቸው ይመስላል። አጼ ምኒልክ የደን የሕግ ማዕቀፍ አውጥተዋል፤ አማካሪም ቀጥረዋል። ፈጥኖ-አደግ የዛፍ ዝርያዎችን ከውጭ አስመጥተዋል። ዛሬ አገሪቷን የተቆጣጠረው አውስትራሊያዊው ባሕር ዛፍ (ኢካሊፕተስ) የትመጣነቱ ዳግማዊ ምኒልክ መሆኑ እሙን ነው። ዳግማዊ ምኒልክ በመንግስት ከሚለማው ደን በተጨማሪ ተራው ዜጋ በባለቤትነት በደን ድነና እንዲሳተፍም አዋጅ አውጥተው እንደነበር የመዕዋለ ዜና ዘጋቢያቸው ፀሀፊ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ ወልደ አረጋይ ዕፈዋል። በአጼ ሃይለስላሴ ዘመን መንግስትም ዛፍ መትከል ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ተግባር እንደነበር ይነገራል።

በደርግ ዘመን የተከሰተው ድርቅና ርሀብ ደግሞ በኢትዮጰያ የችግኝ ተከላ ዘመቻ መንስኤ ሆኗል። በደርግ ስርዓተ መንግስት ችግኝ ተከላ ለችግኝ ተካዩ ማበረታቻ የሚያሰጥ ተግባር ሆኖ እንደነበር ይነገራል። በአካባቢ ጥበቃ ጠንካራ የህግ ማዕቀፎች ተቀርጸው ገቢራዊ ተደርገዋል። በውቅቱ የተደረገው የተራቆቱ አካባቢዎችን በተለይም በተራሮች ችግኝ የመትከል ዘመቻ ፍሬ አፍርቷል። የደርግ ዘመን አረንጓዴ አሻራዎች ዛሬ የተራሮች አረንጓዴ ዕንቁ ሆነዋል።

በዘመነ ኢህአዴግ በአገር ውስጥ ከፍተኛ የደን ውድመት እንደደረሰ ጥናቶች ቢጠቁሙም የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ከደን መመናመንና ከተፈጥሮ ሀብት መራቆት ጋር ተያይዞ አፍሪካና ኢትዮጵያ ያጋጠማቸውን ቀውሶችና ያለባቸውን ተግዳሮቶች ለምዕራቡ ዓለም አስረድተዋል፤ ተሟግተዋልም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በስፋት አረንጓዴ ኢኮኖሚን፣ የአካባቢ ጥበቃንና የተፈጥሮ ሀብት መንከባከብን ትልቅ ትኩረት ሰጥተውታል። በ2011 የክረምው ወቅት ጀምሮ በየዓመቱ ‘አረንጓዴ አሻራ’ ገቢራዊ እያደረጉ ይገኛሉ። በመላ አገሪቱ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች እያሳተፈ መርሃ ግብሩ እንደቀጠለ ነው። ኢትዮጵያን በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረክ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ተምሳሌት ያደረገ ተግባር ነው።

አረንጓዴ ዐሻራ ሲነብር፤ ተስፋን ሲያበስር

“የዛፍ ምስጢሩ ውበቱ ብቻ ሳይሆን፣ ተስፋን ማጫሩ ሕይወትን ማደሱ ነው’’ እንዲሉ የሥነ ሕይወት ሳይንቲስቱ ፕሮፌሰር ለገሰ ነጋሽ፤ ዕጽዋት ማብቀል ዛሬን-አለፍ፣ ትውልድ-ጠቀስ ቁም ነገር ነው። ሰው ችግኝ የሚተክለው ነገን ተስፋ አድርጎ ነው። ተስፋው ዕውን ሲሆን ደግሞ ሕይወቱ በመንፈስም፣ በቁስም ይታደሳል በሚል አምኖ ነው። ዛፍ ተከላ፣ ደን ድነና ደግሞ ተቋማዊ ሲሆን ትርጉሙ የትየለሌ ይሆናል።

ኢትዮጵያ በአራት ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ወጥና መርሐ ግብር ደግሞ ‘በአረንዴ አሻራ’ በማለት ሰይማ ስትሰራ ቆይታለች፤። በ2011 ዓ.ም በክረምቱ መባቻ የተጀመረው አረንጓዴ ዐሻራ ፕሮጀክት ዘንድሮም ለአራተኛ ዙር የሚሆነውን ዝግጅት አገባዷል። ባለፉት ሶስት ዓመታትም ከእቅድ በላይ ችግኞች ተተክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በ2012ቱ የዓለም አካባቢ ቀን በተከበረበት ዕለት “ብዝኃ ሕይወትን መጠበቅና መከባከብ ቅንጦት ሳይሆን ህልውና መሆኑን አይተናል” በማለት የአካባቢ ደህንነት የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል። እንደ ሌላው ክፍላተ ዓለም ሁሉ ኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ መራቆት ችግር ተጋርጦባታል፤ ለጎርፍ አደጋ፣ ለአፈር መሸርሸር፣ ለደን መመናመንና ለብዝኃ ሕይወት ኪሳራ ተዳርጋለችም ብለዋል። በዚህም በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ 20 ቢሊዮን ዛፎችን ለመትከል ራዕይ እንድትሰንቅ እንዳስገደዳት ተናግረው ነበር።

አረንጓዴ ዐሻራ አንድ:የመጀመሪያው ዙር አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በ2011 በይፋ ጀመረ። በዚህ መርሐ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትሩ 1 ሺ ችግኞችን እንደሚተክሉ ቃል በመግባት ህዝቡን ለዘመቻው አነሳሱ፤ ባለፉ ባገደሙበት ሁሉ ችግኝ ተከላን ስራዬ ብለው ተያያዙት። በመጀመሪያው ዙር መርሃ ግብርም አንድ ሰው 40 ችግኞችን እንዲተክል ተሰልቷል። ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአንድ ጀንበር 200 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ዘመቻ ይፋ ሆነ። ከዚህ ውስጥም በአንድ ጀምበር ከ200 ሚሊየን የመትከል ዕቅድ ግቡን አልፎ በቀን 354 ሚሊዮን ገዳማ ችግኞች መተከላቸው ተበሰረ። ይህም በአንድ ጀምበር 50 ሚሊዮን ችግኞች ከተከለችው ህንድ በኋላ የዓለም ክብረ ወሰን እንደያዘ ስለመሆኑ ተነግሯል። በዚህም ኢትዮጵያ በመጀመሪያው አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ላይ 4 ቢሊየን ችግኞችን ተክላለች። 20 ሚልዮን ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ዐሻራቸውን አንብረዋል። በአጠቃላይ ከተተከሉ ችግኞች ደግሞ 84 በመቶ ስለመጽደቃቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሁለተኛውን ዙር አረንጋዴ ዐሻራን ሲያስጀምሩ ገልጸው ነበር።

አረንጓዴ ዐሻራ ሁለት:በሁለተኛው ዙር (በ2012 ዓ.ም) በሀገር አቀፍ ደረጃ ከመጀመሪያው ዙር በአንድ ቢሊየን ብልጫ ኖሮት አምስት ቢሊየን ችግኞችን ተክላለች። ኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ቢኖርም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ርቀታችንን ጠብቀን፣ በግለሰብና በቤተሰብ ደረጃ፣ ከንክኪና ትፍፍግ ርቀን አረንጓዴ አሻራ እናሳርፍ፤ ራሳችንን ከኮሮና ምድራችንን ከአየር መዛባት እንታደግ” በሚል ጥሪ አቅርበው ነበር። በሁለተኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ በተለይ የፍራፍሬ ተክሎች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል። በዚህ ዙር ከተተከሉ 5 ቢሊየን ችግኞች ውስጥ 80 በመቶ መጽደቁንም የመርሃ ግሩ አስፈጻሚ ተቋማት ሲገልጹ ተሰምቷል። በዚህም የሁለት ተከታታይ ዓመታት የ4 እና 5 ቢሊየን ችግኞችን የመትከል ስኬት ዓለም አቀፍ ትኩረት መሳብ ችሏል።

አረንጓዴ ዐሻራ ሶስት:በአምናው የሶስተኛ ዙር አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 6 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ነበር ወደተግባር የተገባው። ከሰሞኑም ‘የኢትዮጵያን እናልብሳት’ በሚል መሪ ሃሳብ የተተገበረው ሶስተኛው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እንደቀደሙት ሁሉ ስኬታማ ነበር። አረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ሳይሆን ባሕል ሆኖ መቀጠል ይገባዋል የሚል ጥሪም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ቀርቧል። በርግጥም ተፈጥሮን ያጎሳቆለ የሰው ልጅ በአየር ንብረት ለውጥ ራሱ መጎሳቆሉ አይቀሬ ነውና ተፈጥሮን መጠበቅ፣ ያጠየመውን ገጸ-መሬት መካስ ግድ ይለዋል።

የአምናውን አረንጓዴ አሻራ ለየት የሚያደርገው ድንበር ተሻጋሪ መሆኑ ነው። ችግኞችን ለጎረቤት አገራት ለመስጠት ታቅዶ ተሰርቷል። ኢትዮጰያ በምስራቅ አፍሪቃ ከሚገኙ አገራት በተለዬ ከፍተኛ ቦታዎች ያሏት(ከበርሃ እስከ ጮቄ የአየር ንብረት ባሌት) ናት። በአንጻሩ አብዛኞቹ ጎረቤቶቿ በርሃማ የአየር ንብረት ባለቤት ናቸው። የአካባቢ ተጽዕኖ (በርሃማነት፣ ድርቅና ጎርፍ) ድንበር ስለማያግደው አካባቢን በቅንጀት ማልማት እንደሚገባ ሳይንቲስቶች ይመክራሉ። የኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ችግኞችን መለገሷ ቅቡልነትን አስገኝቶላታል። ደንን በማልማት ጤናማ አካባቢ በመፍጠር ከጎረቤት አገራት ጋር የሚኖርን ሰላምን ለማረጋገጥም ያግዛል።

አረንጓዴ ዐሻራ አራት:የዘንድሮው አራተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በያዝነው ወር አጋማሽ ላይ ይጀመራል። የአረንጓዴ አሻራ ስራ በዓመታት ተገድቦ የሚሰራ እንዳይደለ እርግጥ ነው።ይሁን እንጂ በ2011 ዓ.ም የመጀመሪያው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሲበሰር በአራት ዓመታት 20 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ተወጥኖ እንደነበር ይታወሳል። ባለፉት ሶስት የአረንጓዴ አሻራ ዓመታትም ከ18 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። የብሔራዊ አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ በዘንድሮው መርኃ ግብር  ከ6 ነጥብ 3 ቢሊየን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው ከ500 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።

የዐረንጓዴ ዐሻራ አገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ

የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሸቲቭ የአገራችን የነገ እጣ ፈንታ የሚወስን፣ ጊዜውን የሚዋጅ ተግባር ነው። ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የተቸረችው አየር ንብረትና መልክዓ ምድር ለዚህ የሚጋብዝ ነው። ደን ልማት ዘላቂ ስራ መሆን አለበት። ባለቤትነት እንዲጨምርም በወል መሬት ብቻ ሳይሆን በግል ይዞታም አረንጓዴ አሻራ መንበር አለበት። የደን ልማት አካል የሆነው አረንጓዴ ዐሻራ አገራዊ ፋይዳው ሁለንተናዊ ነው። አገራዊ ፋይዳው ባለፈው ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ በረከቶችን ተሸክሟል።

እንደ አገር ሲታሰብ መሰረቷ በተለይም በዝናብ ላይ የተመሰረተ ግብርና ለሆነው ኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ተራሮች ደን መልበስ አለባቸው። ደኖች ዝናብ ይስባሉ፣ ውሃ ወደ ከርሰ ምድር እንዲሰርግ ያደርጋሉ። ደኖች ለትነት መቀነሻ መሳሪያም ናቸው። ኢትዮጵያ በቂ ውሃ ባመረተች ቁጥር በቂ ውሃ ትይዛለች፤ በግድቦቿ። በግድቦቿ በቂ ሃይል ካመረተች ለጎረቤት በቂ ሃይል ታቀርባለች፤ ተፈላጊነቷ ክፍ እያለ ይሄዳል። በተቃራኒው በደን አለመኖር የአካባቢ መራቆት ለም አፈሩ እየታጠበ ምርታማነት እየቀነሰ ገበሬውን ያደኸያል፤ ግድቦችንም በደለል ይሞላል።

ኢትዮጵያ ከቆዳ ስፋቷ ከግማሽ በላይ ለደን ልማት የሚውል የተራቆተ መሬት አላት። ለግብርናው፣ ኢነርጂው፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪው መሰረቱ ደን ነው። በተራሮችና ከፍተኛ ቦታዎች የደን ልማት ከሌለለ በከተሞች፣ ግብርናው፣ የሃይል ግድባችን ደህንነት፣… በአጠቃለይ ኢኮኖሚው እጣ ፈንታው ስጋት ውስጥ ስለሚወድቅ አረንጓዴ ዐሻራ የሕልውና ጉዳይ ይሆናል። በዚህም የደን ሀብት ለአገር ኢኮኖሚ ዋልታ በመሆኑ አገራዊ አጀንዳ ተደርጓል።

ረንጓዴ ዐሻራ ቀጣናዊ ፋይዳውም ጉልህ ነው። የኢትዮጵየ ወንዞች ድንበር ተሻጋሪ ናቸው። እነዚህ ወንዞች ውሃ የሚያገኙት ከኢትዮጵያ ተራሮች ከሚገኘው ደን እየታለበ ነው። ይህም ማለት ለቀጣናው አገሮች የውሃ መሰረቶች የኢትዮጵያ ተራሮችና ደኖች ናቸው። እጅግ አንገብጋቢ የሆነው የውሃ ፍሰት ጉዳይ ከተጠበቀ ደግሞ በቀጣናው አገራት መካከል ግጭት እንዳይኖር ያስችላል። ስለዚህ አረንጓዴ አሻራ ለቀጣናችን ሰላምና ደህንነት፣ ስደት እንዲቀንስ፣ የሙቀት አማቂ ጋዝ እንዲቀንስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ከጎረቤቶቿ ከፍታ የሆነቺው ኢትዮጵያ የውሃ ማማ አድርገቷል። የውሃ ማማነቷ የሚጠበቀው ደግሞ ተራሮች ወይም ውሃማ አካላት ዘላቂ አካባቢያዊ ጥበቃ ሲደረግላቸው መሆኑ ሀቅ ነው። ለዚህ ደግሞ የቀጣናውና የታችኛው ተፋሰስ አገራት ከኢትዮጵያ ጎን ሆነው የአረንዴ አሻራቸውን በማንበር ለጋራ ጥቅም ዘብ መቆም ይገባቸዋል።

ሌላው ዓለም አቀፋዊ ፋይዳው ነው። የደን ልማት የጋራ ሃላፊነት ነው። ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ፋይዳው ድንበር ዘለል ነው። የአካባቢ፣ ደን ልማትና አየር ንብረት ጉዳይ በተመድ በዓለም አቀፍ መደረክ አጀንዳ ከሆነ ሰነባብቷል። ከብዙ አስርት ዓመታት በፊት ጀምሩ ጉዳዩ በዓለም አቀፍ መድረኮች ሳይንሳዊ ጥናቶች እየቀረቡ ውይይቶች ተደርገዋል። ሳይንቲስቶችም ፕላኔታችን አደጋ ላይ በመውደቋ የአገራት መግስታት መፍትሔ እንዲያበጁ፣ በደን ልማትና አካባቢ ጥበቃ እንዲያተኩሩ ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግበር ለዓለም አቀፍ ሳይንቲስቶች ጥሪ በቂ ምላሽ ይመስላል። ኢትዮጵያ ያላት የደን ሀብት ቢወድም 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ቶል ካርበን ዳይ ኦክሳይድ ወደ አየር ይለቀቃል። ስለዚህ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ ወደ ደን ድነናና ጥበቃ ዘመቻ መግባቷ  ከፍ ያለ ሚና እየተጫወተች መሆኑን ያሳያል።

በርግጥ ኢትዮጵያ ቀደም ሲልም ለአየር ንብረት የማይበገር ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ቀርጻ ወደተግባር በመግባቷ የበለፀጉ አገራትም በዘርፉ ድጋፋቸውን ሲሰጡ ቆይተዋል። የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ የራሷን ልማትና ዕድገት ከማፋጠን ባለፈ ለዓለም ሥጋት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከልና አደጋዎቹን ለመቀነስ ለጋራ ጥቅም የሚኖረው አስተዋፅዖ ጉልህ መሆኑ ታምኖበታል። ተፈጥሮን ከመንከባከብና ተጠቃሚ ከመሆን በተጨማሪ ለብክለትና ለውድመት ከሚዳርጉ አደጋዎች ጠብቆ ለማቆየት ሁነኛ መፍትሔ ያዘለ ሆኗል-አረንጓዴ ልማት፡፡

ድሕረ ነገር!

በኢትዮጵያ በየክረምቱ በዘመቻ ችግኝ መትከል የተለመደ ነው። የአፈርን በነፋስና በጎርፍ መከላት በመከላከልና የአየር ጠባይ ሚዛንን በመጠበቅ የዛፎች ሚና ወሳኝ ነውና በዘመቻው ከአመራሩ እስከ ተርታው ዜጋ በስፋት ተንቀሳቅሷል። ዐረንጓዴ ዐሻራ በደን መመናመን ደዌ ለተጠቃችው ኢትዮጵያ ፍቱን መድሃኒት ተደርጎ ተወስዷል።

ተፈጥሮ ለፍጡራን ሕልውና መሰረት ነው። እናም ፍጡራን መሰረታቸውን መናድ አይገባቸውም። አምላክ በምክንያት ያነበረውን ውብ ተፈጥሮ ማዛባት ሳይሆን አስውቦ መጠቀም፣ ጠብቆ ማሻገር ግድ ይላል። ከዓለም የተፈጥሮ ሀብት ተቋም ጥናት መሰረት 54 ሚሊየን ሄክታር መሬት የተፈጥሮ ሀብት እንክብካባቤ የሚጠይቅ የተራቆተ መሬት ያለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 11 ሚሊየን በአስቸኳይ ሊለማ የሚገባው መሆኑን ጥናቱ ጠቁሟል። ደን ልማት የቅንጦት ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ነው የሚሰኘውም ለዚህ ነው። ይህን ደግሞ ሰፊ ጉለበት ያለውን ህብረተሰብ በዘመቻ መልክ አስተባብሮ ገቢራዊ ማድረግ ይቻላል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ብዛት ብቻ ሳይሆን ጥራት ወሳኝ ነው። ዘምቶ መትከል ብቻ ሳይሆን ኮትኩቶ ማሳደግ ልብ ሊባል ይገባል። መመሪያ መራሽ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ያሻል። ደን ልማትን በመንግስት ደረጃ ብቻ ሳይሆን በግለሰቦችም መተግበር የሚችል አዋጭ የኢንቨስትመንት አማራጭ ነው።

አረንጓዴ ገጽታ የገነት ምሳሌ ነው፤ ሐመልማላዊ ደን እስትንፋስ ነው፤ ደን ፋይዳው አካባቢያዊ ነው፤ ለድርቅ ክትባት ነው፤ ደን ለገጸ ምድርና ከርሰ ምድር ውሃ ፍሰትን ዘለቂነት ዋስትና ነው፤ ደን ለአፈር መሸርሸር ደጀን ነው፤ ደን ልማት ለተራቆቱት መልክዓ ምድሮች ገመና ልብስ ነው፤ ደን ከሰሩበትም እንጀራ ነው። ሲጠቃለል ደን የሰውና እንስሳት ሕልውና መሰረት ነው። በርግጥም የአገሬ፣ የምድረ ቀደምቷ መልክዓ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ጃኖ መልበስ አለበት!!

 ዐረንጓዴ ዐሻራ ሲነብር፣ ተስፋ ይበሰራል!!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም