በአዲሱ አመት ድህነትን ለመደምሰስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፍቅርና በመደመር ተባብሮ ሊሰራ ይገባል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

98
አዲስ አበባ ጳጉሜ 5/2010 በአዲሱ አመት ድህነትን ለመደምሰስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ በፍቅርና በመደመር ተባብሮ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በፍቅር እንደመር፣ በይቅርታ እንሻገር" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ባለው አዲስ ዘመን ማብሰሪያ መርሃ-ግብር ላይ ፕሮግራም ላይ የእንኳን አደረሳቹ መልእክት አስተላልፈዋል። በጋራ ለተሟላ ነጻነት፣ በህብረት፣ በእውቀት ብርሃን ድህነትን ለመደምሰስ በሰከነ የፖለቲካ እሳቤ ሁሉም ለአገሩ በአንድነት መቆም ይኖርበታል ብለዋል። በጠነከረ ማህበራዊ ትስስር መልካም ጅማሮዎችን ተቋማዊ በማድረግ ዘልማዳዊ አሰራሮችን ስርአት ማስያዝ እንደሚገባም ጠቁመዋል። በመሆኑም መጪው አዲስ አመት የራሳችን አጥርና ቤት የሌለን ሆነን በጋራ ኢትዮጵያን ለመገንባትና አንድነቷን ለመጠበቅ ቁርጠኛ የምንሆንበት ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት። በመሆኑም በአገሪቱ እውነተኛና ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ተከባብረን አንዳችን ለሌላችን ድጋፍ ሆነን ለጋራ ለውጥ መተባበር ያስፈልጋልም ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም