የትምህርት ተቋማት የታለመላቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ ኅብረተሰቡ ሊጠብቃቸው ይገባል- ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው

214

ሀዋሳ፤ ሰኔ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) የትምህርት ተቋማት የታለመላቸውን አገልግሎት በዘላቂነት መስጠት እንዲችሉ ህብረተሰቡ ሊጠብቃቸውና ሊንከባከባቸው እንደሚገባ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው አስገነዘቡ።

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በሲዳማ ክልል ሆኮ ወረዳ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባው የኦዲ ቦኮ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት ዛሬ ተመርቋል፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዐቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ፣ሚኒስትሮች ፣ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ተገኝተዋል።

በዚህ ወቅት ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው "የትምህርት ቤቱ ግንባታ ተጠናቆ ከአካባቢው ህዝብ ጋር በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በመገናኘታችን ተደስተናል " ብለዋል።ህብረተሰቡ ትምህርት ቤቱን በባለቤትነት መንፈስ ጠብቆና ተንከባክቦ ለትውልድ ማሻገር እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።

የትምህርት ተቋማት የታለመላቸውን አገልግሎት በዘላቂነት መስጠት እንዲችሉም ህብረተሰቡ ሊጠብቃቸውና ሊንከባከባቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።ወላጆች ልጆቻቸውን በተለይም ደግሞ ሴቶችን ወደ ትምህርት ቤት መላክና ተምረው ለቁምነገር እንዲበቁ ማበረታታት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው በአካባቢው ሰፊ የመሠሰተ ልማት ችግር እንዳለ ከህዝቡ ጋር በተለያዩ ጊዜያት በነበሩ ውይይቶች መነሳቱን አስታውሰዋል።

የክልሉ መንግስት ህዝቡ ያነሳቸውን የመንገድ፣ የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገልጸው የኦዲ ቦኮ ቀበሌን ከሆኮ ወረዳ ማዕከል የሚያገናኝ አዲስ የጠጠር መንገድ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

"የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ያስገነባው ትምህርት ቤት የአካባቢውን ነዋሪዎች አንገብጋቢ ጥያቄ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመለሰና ህዝብን ተጠቃሚ ለሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ትልቅ እገዛ ያደርጋል" ብለዋል።

ትምህርት ቤቱ የተገነባበት የኦዲ ቦኮ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ አዲሱ ሌንጂሾ አካባቢያቸው በመሠረተ ልማት ወደኋላ የቀረ እንደሆነ ገልፀዋል።

"አሁን ላይ ችግሮቻችን ተመልካች በማግኘታቸውና የዚህ እድል ተጠቃሚ በመሆናችን እጅግ ተደስተናል" ብለው "መንግስት ለህዝብ ጥያቄ እስከታች ድረስ ወርዶ ለመመለስ ያሳየው ጥረት በዘላቂነት እንዲሳካ በገንዘብም ሆነ በጉልበታችን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ስጦታ ሌዳሞ በበኩሉ የትምህርት ቤቱ መገንባት ከዚህ በፊት ወንድሞቹ እስከ 15 ኪሎ ሜትር ርቀው በመሄድ በአጎራባች ወረዳዎች በመማር ያሳለፉትን እንግልት ስለሚያስቀር መደሰቱን ገልጻል።

በቀጣይ ዓመት የአዱሱ ትምህት ቤት ተማሪ ለመሆን በጉጉትና በትጋት እየተማረ እንደሚገኝም ተናግሯል።

ትምህርት ቤቱ አምስት ሕንፃዎች እንዳሉትና 12 መማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ ሙከራ ፣ቤተ መጽሐፍት፣ የተማሪ ክሊኒክ፣ የአስተዳደር አገልግሎት መስጫ ፣ መሰብሰቢያ አዳራሽና የመፀዳጃ ቤት ያካተተ መሆኑ ተመላክቷል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም