በደቡብ ክልል አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ወደ ኢንዱስትሪ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

104

ሶዶ፣ ሰኔ 11/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ወደ ኢንዱስትሪ ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ገለጹ።

በክልሉ ከፍተኛ ካፒታል በማስመዝገብ ወደ ኢንዱስትሪ የተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች የእውቅናና ሽልማት መርሐ ግብር በወላይታ ሶዶ ተካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ከ134 በላይ ለሚሆኑ ሞዴል ኢንተርፕራይዞች እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍ በተሰራው ሥራ ውጤት መጥቷል።

ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ለመተካት የተደረገው ጥረት ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረው፤ የክልሉ መንግስት ለዘርፉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።

ክልሉ ለስራ ምቹ መሆኑን አመልክተው፣ ዜጎች የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ተፈጥሮን ወደ ሀብት ሊቀይሩ ይገባል ብለዋል።

”ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ባህላችንን ማዳበር አለብን ” ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ እንደ ሀገር የታለመውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት በልማት ስራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የተፈጥሮ ሀብትን እንደ እድል በመጠቀም የተጀመረውን ልማት ከግብ ለማድረስ የክልሉ ሕዝብ ጥረት እንዲያደርግ አሳስበዋል።

የደቡብ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢረጋ ብርሃኑ በበኩላቸው በመርሐ ግብሩ በከተማና በገጠር ስራ ዕድል ፈጠራና በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ዘርፍ ሞዴል ለሆኑ 134 በላይ ኢንተርፕራይዞች ዕውቅና ሽልማት መሰጠቱን አስታውቀዋል።

ለዕውቅናና ሽልማት ከበቁት መካከል ባስመዘገቡት ካፒታልና በፈጠሩት የስራ ዕድል መነሻ ከአነስተኛ ወደ ታዳጊ መካከለኛ እንዲሁም ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪነት የተሸጋገሩ 16 ኢንዱስትሪዎች ይገኙበታል ብለዋል።

ዘርፉ የስራ እድል በማመቻቸት ዜጎች ከራሳቸው አልፈው የሀገርን ኢኮኖሚ የሚያሳድጉበት መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ በዚህም ባለፉት 11 ወራት ከ300 ሺህ በላይ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ ስራ እንደተፈጠረላቸው አስታውቀዋል።

ለኢንተርፕራይዞች 798 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር በብድር መቅረቡን አመልክተው፤ ለኢንተርፕራይዞች የተመቻቸውን የሀገር ውስጥ የገበያ ትስስር ከ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ በማድረስ እቅዱን ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

ኢንተርፕራይዞቹ ምርታቸውን በቀጥታ ለሸማቾች በማድረስ የህብረተሰቡን የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ማገዛቸውን አስረድተዋል።

የኢንተርፕራይዞች ልማት ዘርፍ ዜጎችን ከስራ ጠባቂነት በማላቀቅ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

በክልሉ መንግስትና በስራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት ለዘርፉ ልማት ከፍተኛ ትኩረትና ድጋፍ መሰጠቱን ገልጸው፤ የሴክተሩ አመራሮችና ባለሙያዎች ለተግባራዊነቱ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በዝግጅቱ ላይ የደቡብ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ሰርሞሎ፣የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ይገዙ፣የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜ፣ የክልሉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ