የመዲናዋ ነዋሪዎች የውሃ ማፋሰሻዎችን በማጽዳት በክረምት ወቅት የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት ከወዲሁ መከላከል አለባቸው

128

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመዲናዋ ነዋሪዎች የውሃ ማፋሰሻዎችን በማጽዳት በክረምት ወቅት የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት ከወዲሁ መከላከል እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ምክትል ከንቲባው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 በመገኘት የክረምት የጽዳት ንቅናቄ መርሃ-ግብር አስጀምረዋል፡፡

በዚህም በመዲናዋ ክረምት ከመግባቱ በፊት  የጎርፍ መውረጃ ቦዮችንና ቱቦዎችን አጽድቶ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ሥራ በተደራጀ መልኩ የተጀመረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሕብረተሰቡ በቆሻሻ የተሞሉ የፍሳሽ መውረጃ መስመሮችን በማጽዳት በክረምት የሚዘንብን ውሃ ወደ ወንዝ እንዲገባ በማድረግ ሁሉም ነዋሪ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

ወደ ወንዞች የሚገቡ ውሃዎች በተፈጠረላቸው መሰረተ-ልማቶች ብቻ እንዲፈሱ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የመዲናዋ ነዋሪዎች የክረምት ወራት ከመጀመሩ ቀደም ብለው ይህን በማድረግ በህይወትና በንብረት ላይ የሚደርሰውን አደጋ መከላከል ይገባል ብለዋል፡፡

የጽዳት ሥራ በንቅናቄ ብቻ የሚሰራ ሳይሆን የእለት ተለት ተግባር መሆን እንዳለበትም ምክትል ከንቲባው አስገንዝበዋል

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽታዬ መሐመድ በበኩላቸው፤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በሳምንት ሦስት ቀን የጽዳት ዘመቻ በብሎክ ደረጃ እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በዚህም በርካታ ብሎኮችን ንጹህና ጽዱ ከማድረግ ባለፈም በመንገድ መሰረተ-ልማት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት የመከላከል ሥራ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በተያዘው ክረምትም ለጎርፍ ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉ አካባቢዎችን በመለየት እና የፍሳሽ መውረጃ መስመሮችን በማጽዳት የቅድመ-መከላከል ዝግጅት በንቅናቄ የተጀመረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በክፍለ ከተማው በርካታ የውሃ ማፋሰሻ ቱቦዎች በቆሻሻ የመደፈን ችግር በመኖሩ ክፍለ ከተማው በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ነዋሪው እነዚህን ቱቦዎች በማጽዳት ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም