በሳይንስና ቴክኖሎጂ የበለፀገች ሀገር ለመገንባት ለፈጠራ ስራ የሚደረገው ድጋፍ ሊጠናከር ይገባል

290

ሰኔ 11/2014 (ኢዜአ) በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የበለፀገች ሀገር ለመገንባት ለወጣቶች የፈጠራ ስራ የሚደረገው ድጋፍ መጠናከር እንዳለበት በአዲስ አበባ ከተማ የተማሪዎች የሳይንስና የፈጠራ አውደ-ርዕይ የተሳተፉ ተማሪዎች ገለጹ፡፡

የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የብልጽግና ጉዟችንን በሳይንስ ፈጠራ ሥራ እውን እናደርጋለን!” በሚል መሪ ሃሳብ በወዳጅነት ፓርክ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 7ኛው የአዲስ አበባ ከተማ አቀፍ የተማሪዎች የሳይንስና የፈጠራ አውደ-ርዕይ ተጠናቅቋል፡፡

በአውደ-ርዕዩ ላይ የተሳተፉ ተማሪዎች ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን በፈጠራ ስራ እንዲሳተፉ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

በዚህም በክህሎቱ የዳበረ ትውልድ በማፍራት በሳይንስና ቴክኖሎጂ የበለጸገች አገር መገንባት እንደሚቻል ነው የገለጹት፡፡

በአውደ ርእዩ ላይ የኪነ ጥበብ የፈጠራ ውጤቶችን ይዞ የቀረበው ተማሪ ቦንሳ መለስ በሳይንስ ፈጠራ ስራ ላይ ለመሰማራት በርካታ ተማሪዎች ፍላጎትና አቅም ቢኖራቸውም የግብዓትና የዕውቀት ድጋፍ  በበቂ ሁኔታ እንድማያገኙ ጠቁሟል።

ይህም ታዳጊዎችና ወጣቶች ለሀገራቸው የሚያደርጉት አስተዋፅኦ ውስን እንዲሆን ድረጓል ነው ያለው።

የተሻለ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ተማሪዎች  በመለየት በበጀትና በዕውቀት በመደገፍ ለህዝብና ሀገር የሚጠቅሙ የፈጠራ ውጤቶችን  ማምረት እንደሚቻል በማንሳት።

ተማሪ ፋሲል ኡርጌቻ በአውደ ርዕዩ ላይ ሮኬት፣ ተንቀሳቃሽ ሆስፒታል፣ መኪና እና የመድፍ ሞዴል ያቀረበ ሲሆን፤

በኢትዮጵያ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን ለውጤት ለማብቃት ትብብርና ድጋፍ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ተማሪ መርሲማ ኤርዴሳ በበኩሉ በአርቴፊሻል ኢንተለጀስ ዘርፍ ለሀገር ደህንነት አገልገሎት የሚሰጥ መሳሪያና ሌሎች የፈጠራ ስራዎችን ከጓደኞቹ ጋር አቅርቧል፡፡

የፈጠራ ስራዎቹ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለመደገፍ እና የግብርናን ዘርፍ ለማዘመን የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የአርቴፊሻል  ኢንቴሌጀንስ ዘርፍ ሀገሩን የሚጠቅም ስራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ነው የገለጸው፡፡

በ7ኛው አውድ ርዕይ ላይ የተሻለ የፈጠራ ስራ ካቀረቡ ተማሪዎች መካከል የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የአርተፊሻል ኢንተሌጀንስ ማዕከል ለስምንት ተማሪዎች ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡