ጋዜጠኞች የሙያ ስነ-ምግባርና የኢትዮጵያን ሕጎች አክብረው ሥራቸውን በኃላፊነት ማከናወን ይጠበቅባቸዋል

111

ሰኔ 11/2014 (ኢዜአ) ጋዜጠኞች የሙያ ስነ-ምግባርና የኢትዮጵያን ሕጎችን አክብረው ሥራቸውን በኃላፊነት ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

ጋዜጠኝነት ሁሉንም ርዕሰ ጉዳይ የሚዳስስ ሙያ ቢሆንም ሊከተላቸው የሚገቡ መርህና የሙያ ስነ-ምግባር ድንጋጌዎች አሉት።

በዚህም ጋዜጠኝነት ለሙያው መርሆች የሚገዛና ከወገንተኝነት በጸዳ መልኩ ትክክለኛ መረጃን ለሕዝብ የሚያደርስ ሙያ ቢሆንም በኢትዮጵያ ይህ የሙያ ስነ-ምግባር በተደጋጋሚ ሲጣስ ይስተዋላል፡፡

በተለይ በጋዜጠኝነት ሽፋን የፖለቲካ አቋምን ማራመድ፤ እንዲሁም ለአንድ ወገን ብቻ በመወገን የመዘገብ ዝንባሌዎች በተደጋጋሚ ይፈጸማሉ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በጋዜጠኝነት ሽፋን የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚሰሩ አካላት መበራከታቸውን ጠቅሰው፤ ይህም ሕገ-ወጥ አካሄድ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የፕሮግራም ዘርፍ ዳይሬክተር አዳም ታደሰ፤ ጋዜጠኝነት የሙያ ስነ-ምግባር ያለውና መብቶችና ግዴታዎችን በማክበር የሚሰራ ሙያ መሆኑን ይናገራል፡፡

ጋዜጠኛ ወገንተኝነቱ ለእውነት መሆን እንዳለበት ገልጾ፤ ከዚህ አኳያ ጋዜጠኞች ስሜታቸውን በሥራቸው ላይ ማንጸባረቅ የለባቸውም ነው ያለው፡፡ጋዜጠኞች ያሉበትን ማንነትና ቡድን ወደጎን ትተው በገለልተኝነት ሥራቸውን ማከናወን እንደሚጠበቅባቸውም አስረድቷል።

ጋዜጠኞች የማኅበረሰብ አንቂ (አክቲቪስት) ወይም ፖለቲከኛ ባለመሆናቸው በሚዛናዊነት ሕዝብን ማገልገል ይጠበቅባቸዋል ብሏል፡፡

ጋዜጠኞች የሙያ ስነ-ምግባርን አክብረው ሥራቸውን እንዲከውኑ የሙያ ማህበራት ተጠናክረው መሥራት እንዳለባቸውና መንግሥትም ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበትም ነው የገለጸው፡፡

የድሬ ቲዩብ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ፍሬው አበበ በበኩሉ፤ ጋዜጠኝነት ገለልተኛ በመሆን መሥራትን የሚጠይቅ እንጂ እንደ አክቲቪስት ወገንተኝነት የሚንፀባረቅበት ሙያ አለመሆኑን ገልጿል።

"በአገሪቱ ማህበራዊ አንቂነትና ጋዜጠኝነት ተቀላቅሎ ሲተገበር ይስተዋላል" ያለው ጋዜጠኛ ፍሬው፤ ጋዜጠኞች የሙያን ሰነ-ምግባርና የአገሪቱን ሕጎች አክብረው ሥራቸውን ማከናወን አለባቸው ነው ያለው፡፡

ከዚህ አኳያ ጋዜጠኞች ጥፋት ሲፈጽሙ በሕግ መጠየቅ እንዳለባቸው ነው የገለጸው፡፡ መንግሥት ከጋዜጠኞች ሙያ ማህበራትና የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ባልተገባ ድርጊት የተሰማሩ መገናኛ ብዙኃንን መለየትና መልካም የሰሩትን ማበረታታት እንደሚጠበቅበት የተናገረው ደግሞ የአሃዱ ሬድዮና ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥበቡ በለጠ ነው።

መንግሥት የጥላቻ ንግግርና አፍራሽ ተግባር ላይ የተሰማሩ መገናኛ ብዙኃንን ያልተገባ ተግባር ለማረም ከዘርፉ ምሁራንና ባለሙያዎች ጋር ተባብሮ መሥራት እንዳለበትም አክሏል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም