በምርትና አገልግሎት ጥራት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ለማረም የሚዲያ ባለሙያዎች ዕገዛ ወሳኝ ነው

73

አዳማ ኢዜአ ሰኔ 11/2014...በምርትና አገልግሎት ጥራትና በደረጃዎች አተገባበር ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም የሚዲያ ባለሙያዎች ዕገዛ ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ከመንግሥትና ከግል የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች የተሳተፉበት መድረክ በአዳማ ተካሂዷል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት በቀለ እንደገለጹት የሀገራችን የምርት ጥራትና ደረጃዎችን በማሳደግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከ12 ሺህ በላይ ደረጃዎች ተዘጋጅተዋል።

በተለይ የሰብል፣ ጥራጥሬ፣ የኢንዱስትሪ ምርቶች፣ ማር፣ በርበሬ፣ ሽሮ፣ ቆሎ፣ የእንስሳት ተዋፅዖን ጨምሮ በልዩ ሁኔታ 436 ደረጃዎች መዘጋጀቱንም ተናግሯል።

ከተዘጋጁት ደረጃዎች ውስጥ 296 የሚሆኑት አስገዳጅ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሯ ዶክተር መሰረት በቀለ ገልጸዋል።

በዚህም የሀገራችን የግብርና እና ኢንዱስትሪ ምርቶች ከመሰረቱ ጀምሮ የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲመረቱና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነትና ተቀባይነት ለማስፋት እየሰራ ነው ብለዋል።

ግብርና፣ ጨርቃጨርቅ፣ ኬሚካልና የኬሚካል ውጤቶች፣ ኤሌክትሮኒክስና የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች፣ ንግድ፣ ግንባታ፣ የአካባቢ ጤናን ጨምሮ ለአጠቃላይ ምርቶችና አገልግሎቶች ደረጃዎች እየተዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል።

በደረጃዎች አተገባበርና አፈፃፀም ላይ ሰፊ ክፍተት መኖሩን ገልጸው፤ ማነቆዎችና የግንዛቤ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚዲያ ባለሙያዎች ሚና የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ማህበረሰቡ ስለደረጃዎች ፋይዳ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው፣ ለምርትና አገልግሎት ጥራት የድርሻውን እንዲወጣ ማስቻል ከሚዲያ ባለሙያዎች የሚጠበቅ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን አስገንዝበዋል።

የሚዲያ ተቋማትና ባለሙያዎች ደረጃዎችን ለህብረተሰቡ በተገቢው መንገድ በማስተዋወቅና በአተገባበር ላይ የሚታዩ ክፍተቶች እንዲታረሙ ሚዲያዎች በሙሉ አቅማቸው ሊያግዙን ይገባል ብለዋል።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን በበኩላቸው የምርት ጥራት ችግር ለመቅረፍ መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በተለይ የወጭ ንግድ ምርቶች ጥራት ለማስጠበቅ፣ ተወዳዳሪና በገበያው ዘልቆ እንዲገቡ ለማስቻል የምርት ጥራትና ደረጃዎች የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያን የማምረት አቅም ከማጠናከር ባለፈ የምርት ጥራትና ደረጃን በማሳደግ ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ውድድር ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ እንዳለው።

በዚህም የአጠቃላይ ምርት ጥራትና ደረጃዎችን ማዘጋጀትና መተግበር እንደሚገባ ጠቅሰው በደረጃዎች አተገባበርና ጠቀሜታ ላይ ያለውን ክፍተት፣ የአመለካከትና የግንዛቤ እጥረት ለማስወገድ የሚዲያ ባለሙያዎች እገዛ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ኢንስቲትዩት የሀገራችንን የምርትና አገልግሎት ጥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የቤተ ሙከራና ፍተሻ ማዕከላትን ጨምሮ ዘመናዊ የጥራትና ደረጃዎች የስልጠና አካዳሚ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እየገነባ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም የኢንዱስትሪዎች የምርት ጥራት፣ አምራችና አግልግሎት ሰጪ ተቋማት የጥራት ባለቤት ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በጥራትና ደረጃዎች ላይ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት በተገቢው መንገድ ለህብረተሰቡና አምራቾች በማድረስ በኩል ሚዲያዎች የድርሻውን መወጣት አለባቸውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም