የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈጥሮ ሃብትን የማልማት አቅሙ እየጨመረ መምጣቱን ገለጸ

155

አሶሳ፣ ሰኔ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወርቅን ጨምሮ የተፈጥሮ ሀብት የማልማት አቅሙ እየጨመረ መምጣቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ተናገሩ።

"የማዕድን ሃብት ለዘላቂ ልማት" በሚል የክልሉ የማዕድን ዘርፍ ሲምፖዚየም በአሶሳ ከተማ ዛሬ ሲጀምር ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ ክልሉ ለረጅም ጊዜ የፀጥታ ችግር አጋጥሞት ቆይቷል።

የጸጥታ ችግሩ ክልሉን ቢፈትነውም በፈተና ውስጥ ዕድል በመፍጠር የተፈጥሮ ሃብቱን እያለማ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ለአብነትም በ2014 በጀት ዓመት ብቻ 22 ኩንታል ወርቅ ከክልሉ ወደ ብሄራዊ ባንክ ገብቷል ብለዋል።

እንዲሁም 514 ሺህ ቶን የከሰል ድንጋይ እና 164 ሺህ ቶን እምነበረድ በበጀት አመቱ በህጋዊ መንገድ መልማቱን አቶ አሻድሊ አመልክተዋል።

የእውቀት እና የቁጠባ ባህል ማነስ እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብት ክብካቤ ማነስ የዘረፉ ፈታኝ ሁኔታዎች እንደሆኑ ገለጸው፤ በጥናት ላይ ተመስርቶ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ሃብት ይዘን በድህነት የምንቆይበት ጊዜ ማብቃት አለበት ሲሉ አቶ አሻድሊ ገልጸው፤ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ለተፈጥሮ ሃብት ልማት ዘርፍ ጥናት ላይ የተመሰረተ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ከማል አብዱራሂም በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከ2012 ጀምሮ በበርካታ ዘርፎች የልህቀት ማዕከል ሆኖ መለየቱን ጠቅሰው፤ ማዕድን ልማት አንዱ የትኩረቱ መስክ እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም