የአምራች ዜጎችን ህልም እያከሰመ ያለውን የትራፊክ አደጋ የመከላከሉ ስራ አሁንም ትኩረት ይሻል

110

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2014 (ኢዜአ) የአምራች ዜጎችን ህልም እያከሰመ ያለውን የትራፊክ አደጋ የመከላከሉ ስራ አሁንም ትኩረት ይሻል።

ወጣት አብዱልሰላም አህመድ ትውልድ እና እድገቱ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስልጤ ዞን ሲሆን እድሜው 28 ዓመት እንደሆነ ይናገራል፡፡

በልጅነቱ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የተለያዩ የቀን ሥራዎችን በመሥራት ባገኘው አቅም ራሱንና ቤተሰቡን ሲደግፍ መቆየቱን ይገልጻል፡፡

እንደወትሮው የእለት ጉርሱን ለመፈለግ በወጣበት አጋጣሚ በተለምዶ "ዓለም ባንክ" ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በእግረኛ ማቋረጫ ሲሻገር የመኪና አደጋ እንዳጋጠመው ይናገራል፡፡   

አደጋ በደረሰበት ወቅት በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ወደ አቤት ሆስፒታል በመውሰድ ሕክምና እንዲያገኝ እንዳገዙት የሚናገረው ወጣት አብዱልሰላም፤ ኑሮውን ለማሸነፍ በሚሯሯጥበት የወጣትነት እድሜው የደረሰበት የመኪና አደጋ ዓላማውን እንዳሰናከለበት ሕክምናውን ከሚከታተልበት አቤት  ሆስፒታል ሆኖ ለኢዜአ ገልጿል፡፡

የትራፊክ አደጋ የሁሉም ዜጋ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሶ፤ አሽከርካሪዎችም ሆነ እግረኞች ያለምንም መዘናጋት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ነው የተናገረው፡፡

ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተለይ እግረኞች መንገድ በሚያቋርጡበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይመክራል፡፡

ከደረሰበት አደጋ አገግሞ ከሆስፒታል ሲወጣም አደጋው በሌሎች ወገኖች ላይ እንዳይደርስ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የበኩሉን ኃላፊነት እንደሚወጣ ነው የተናገረው፡፡

በአቤት ሆስፒታል የማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል ኃላፊ ተስፋዬ እጅጉ እንዳሉት፤ የትራፊክ አደጋ በሕብረተሰቡ ላይ እንዲሁም በሀገሪቱ ላይ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

ለአደጋው መበራከት በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ ጠቅሰው፤ በተለይ የትራፊክ ሕግን አለማክበርና በአሽከርካሪዎች ዘንድ የሚታየው ቸልተኝነት ችግሩን አባብሶታል ይላሉ፡፡

በተጨማሪ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችም ችግሩን እያባባሱት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአቤት ሆስፒታል በተለያዩ አደጋዎች ሕክምና ለማግኘት ከሚመጡ ታካሚዎች ውስጥ 30 በመቶ የሚሆኑት የትራፊክ አደጋ የደረሰባቸው መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡

በአደጋው ምክንያት ወደ ሆስፒታል ከሚመጡ ታካሚዎች መካከል ከ15 እስከ 49 እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አምራች ኃይሎች በብዛት እንደሚገኙ አክለዋል፡፡

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ ታጠቅ ነጋሽ፤ በሀገሪቱ ለሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር፣ ለእግረኞች ቅድሚያ አለመስጠት፣ የትራፊክ ሕግና ደንብን አለማክበር እና የመንገድ ሁኔታ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ተቋማትን በማዋቀር የበኩሉን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ የቁጥጥር እና ክትትል ሥርዓትን በማጠናከር ከመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ለመቅረፍ  ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም