ሐሰተኛ መረጃዎችን ለማጥራት የሴት ጋዜጠኞች ተሳትፎና አቅም መጠናከር አለበት

131


አዳማ ፤ ሰኔ 11/2014 (ኢዜአ) ሐሰተኛ መረጃዎችን ለማጥራትና መከላከል የሴት ጋዜጠኞች ተሳትፎና አቅም መጠናከር እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ገለፀ።


ለሴት የሚዲያ ባለሙያዎች በጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።


የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሐመድ እንዲሪስ እንደገለፁት በሚዲያ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ ይበልጥ መጠናከር አለበት።


በተለይ በዘርፍ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ያሉ ሴት ሙያተኞችን በትምህርትና አቅም በማብቃትና በመደገፍ የተሻለ ሚና እንዲኖራቸው ማስቻል እንደሚገባ ተናግረዋል ።


በተለይ ሴት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማህበር ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር በጉዳዩ ዙሪያ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።


ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ሴት የዘርፉ ሙያተኞች ሐሰተኛና የተዛባ መረጃን የማጥራት አቅም እንደሚኖራቸው ገልጸው፤ በተለይም በተለይም ሴት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ባለስልጣኑ ተገቢውን ዕገዛ እንደሚያደርግ ተናግርዋል።


የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሴቶች ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ርብቃ ታደሰ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት እየተበራከተ የመጣውን የተዛባ ሐሰተኛ መረጃን ለመከላከልና ለመቋቋም የሚያስችል አቅም መፍጠር አለብን ብለዋል ።


በተለይ የጥላቻ ንግግሮችና ሐሰተኛ መረጃዎች ዙሪያ ሴት የዘርፉ ሙያተኞች በቂ ግንዛቤና ክህሎት እንዲኖራቸው ለማስቻል የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ጠቅሰዋል ።


በዚህም ሐሰተኛ መረጃዎችን የማጥራት አቅም እንዲኖረን ጭምር በዘላቂነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል ።
መድረኩ ለሁለት ቀናት የሚቆይ መሆኑን ከመርሃግብሩ ማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም