በምሥራቅ ወለጋ ከ402 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የአቮካዶ ችግኝ ይተከላል

89

ነቀምቴ ፤ ሰኔ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በምሥራቅ ወለጋ ዞን በዘንድሮው ክረምት ከ402 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የአቮካዶ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉን የዞኑ የግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ ፡፡

የጽህፈት ቤቱ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ባለሙያ አቶ ጋዲሣ ሞሲሳ  የዞኑ የአርሶ አደሮች ከመደበኛ ግብርና በተጓዳኝ አቮካዶን  በኩታ ገጠም  የማልማቱ ሥራ መጀመራቸውን  አስታውቀዋል።

በዞኑ በተያዘው የክረምት ወራት የሚተከሉ 370ሺህ 550 ያህል የአቮካዶ ችግኞች የተዘጋጁ ሲሆን፤ ከመካከላቸው ወደ 173ሺህ 700 የሚጠጉት በተመረጡ 49 ኩታ ገጠም ማሳዎች የማልማት ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች ለችግኞቹ መትከያ ከ74 ሺህ በላይ ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውንና እስካሁን ከ10 ሺህ 400 በላይ የአቡካዶ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ የዋዩ ቱቃ ወረዳ  ግብርና ጽህፈት ቤት የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ባለሙያ አቶ ገመቹ ወጋሪ  እንዳሉት በወረዳው በተመረጡ ስድስት ኩታ ገጠም ማሳዎች 89 ሄክታር መሬት በአቦካዶ ይለማል።

የጉቶ ጊዳ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የአትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያ አቶ ጌታቸው ተስገራ  ለተከላ ከተዘጋጁት 34ሺህ የአቡካዶ ችግኞች በተመረጡ አምስት ኩታ ገጠም ማሰዎች  በ44  ሄክታር መሬት ላይ ለመትክል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

ባለሙያው አክለውም እስካሁን 25ሺህ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች ተዘጋጅተው 7ሺህ 342 የአቡካዶ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።

በምሥራቅ ወለጋ ዞን እካአሁን 564 ሄክታር መሬት በአቡካዶ መልማቱን ከዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።