ሚኒስቴሩ "ኦሪዮን ኤ ኤስ ቲ" ከተሰኘ የአሜሪካ ኩባንያ ጋር በስፔስ ቴክኖሎጂ ዘርፍ በትብብር ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ

104

ሰኔ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር "ኦሪዮን ኤ ኤስ ቲ" ከተሰኘ የአሜሪካ ኩባንያ ጋር በስፔስ ቴክኖሎጂና ሳይንስ ዘርፎች በትብብር መሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ እና የኦሪዮን ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሌክሳንደር አልቪን ናቸው፡፡

በስምምነቱ መሰረትም ተቋማቱ በሳተላይትና ስፔስ ቴክኖሎጂ ዘርፎች በትብብር የሚሰሩ ይሆናል፡፡

የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የስፔስ ቴክኖሎጂን ለፈጣን የተሻለ እና ዘላቂ ልማት ለመጠቀም እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።

ዘርፉን ለኮሙኒኬሽን፣ ለሚቲዎሮሎጂ እንዲሁም ለኤኮ-ቱሪዝም እና ለማዕድን ሥራዎች እየዋለ መሆኑን አንስተው፤ በዚህም ምርምሮችን በማድረግ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዛሬው እለት የተደረገው ስምምነት በዘርፉ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠውና መንግሥትም ዘርፉን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡

የኦሪዮን አፕላይድ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሌክሳንደር አልቪን በበኩላቸው፤ ስምምነቱ ትልቅ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪ ኢትዮጵያ በሕዋ ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪ እንድትሆን እንደሚያግዛት ገልጸው፤ በተለይ በግብርና ውሃ ሃብት ልማትና አደጋ መከላከል ሥራዎችን በማዘመን ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

ኦሪዮን አፕላይድ ሳይንስ ቴክኖሎጂ በሰሜን አሜሪካ ቨርጂኒያ የተመሰረተ ኩባንያ ሲሆን፤ በሕዋ ሳይንስ ኢንዱስትሪ መስክ የማማከር እና የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም