የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ዜጎች በግድቡ ላይ ያላቸውን መብትና ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ነው

171

ሰኔ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚከናወነው የውሃ ሙሌት ዜጎች በግድቡ ላይ ያላቸውን መብትና ባለቤትነት የሚያረጋግጥ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና እስያ ጥናትና ምርምር ማዕከል መምህር ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ ገለጹ።

ዶክተር ሳሙኤል ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያዊያን ግድብ ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዚህም መላው ኢትዮጵያዊያን በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ውስጥ ሆነው እንኳን አሁንም ሳይታክቱ ለግድቡ መጠናቀቅ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የግድቡ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በ2013 ሐምሌ ወር መከናወኑን ያስታወሱት ዶክተር ሳሙኤል፤ ዜጎች ለሦስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ሥራ አስፈላጊውን ድጋፍና ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ሆኖም የህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት እንዳይሞላና ኃይል የማመንጨት ሥራው እንዲስተጓጎል የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት የተለያዩ ዘመቻዎችና ጫናዎች እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ግድቡን የገነባችው ፍትሃዊ የመጠቀም መርህን መሰረት በማድረግ መሆኑን ጠቅሰው፤ከዚህ አኳያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ባለፈ ለቀጣናው ልማት ጉልህ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።ቀጣናውን በኃይል በማስተሳሰርም የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንደሚያጠናክር ነው ያብራሩት፡፡

የዘርፉ ምሁራን፣መገናኛ ብዙኃንና መላው ሕዝብ የመጀመሪያውንና ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በማሳያነት በመጥቀስ የግድቡን ጠቀሜታና እውነታ በማስረዳት መታገል ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

በተለይም የውሃው መሞላት ከኢትዮጵያ አልፎ ለተፋሰሱ አገራትም ጭምር ያለውን ጠቀሜታና ሚና እንደ ቀደመው ጊዜ አጽንኦት በመስጠት ማስገንዘብ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡

''የግድቡ ውሃ ሙሌት ዜጎች በግድቡ ላይ ያላቸውን መብትና ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ነው" ብለዋል።

ሦስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በሚፈለገው መልኩ በማከናወን በአንደኛው ተርባይን የተጀመረውን ኃይል የማመንጨት ተግባር ለማጠናከር መላው ኢትዮጵያዊያን የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዘርፉ ምሁራንና መገናኛ ብዙኃን ሳይንሳዊ እውነቶችን መሰረት በማድረግ ግድቡን በሚመለከት የሚወጡ የተሳሳቱ መረጃዎች ላይ ፈጥነው ምላሽ በመስጠት ዘወትር ሊሰሩ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም