በኢትዮጵያ መንግስት የተወሰነው ሰብዓዊነትን ማዕከል ያደረገ የተኩስ አቁም ሰብዓዊ ድጋፍን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል

106

ሰኔ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ መንግስት የተላለፈው ሰብዓዊነትን ማዕከል ያደረገ የተኩስ አቁም ውሳኔ በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገለጸ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ባስሊ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ባጠናቀቁበት ወቅት እንደገለጹት፤ ባለፉት ሁለት ወራት 2 ሺህ 500 እርዳታ የጫኑ መኪኖች ወደ ትግራይ ገብተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው መጋቢት ወር ተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የክልሉ ነዋሪዎች እርዳታ እየደረሰ መሆኑን አንስተዋል።

ተኩስ አቁሙ በችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን የታደገና በመሆኑ በዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብ አድናቆት እንደተቸረውም ነው ያነሱት።

ዋና ዳይሬክተሩ በድርቅ የተጎዳውን የሶማሌ ክልል መጎብኘታቸውን ጠቅሰው፤ ተደጋጋሚ ድርቅ፣ ግጭት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትና ችግር አባብሶታል ነው ያሉት።

በአገሪቷ የተለያዩ ችግሮች በመከሰታቸው በበርካታ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የእለት ደራሽ ምግብ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር አንጻር  ቀድሞ ሲያከፋፍል የነበረውን ድጋፍ ለመቀነስ መገደዱን አንስተዋል።

ዓለም ዓቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የጠየቁት።

በኢትዮጵያ ያለው ተደጋጋሚ ድርቅና የአየር ንብረት ለውጥ በርካታ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊ እንዲሆኑ አድርጓል ያሉት ደግሞ የስዊዲን ዓለም ዓቀፍ ትብብር ሚኒስትር ማቲልዳ ኤርንካራንስ ናቸው።

መንግስታቸው ኢትዮጵያውያንን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ስዊድን በኢትዮጵያ የምትተገብረውን የአምስት ዓመት የልማት ስትራቴጂ እንዳዘጋጀች ገልጸዋል።

የልማት ስትራቴጂው በየዓመቱ የ35 ሚሊዮን ዶላር በጀት ያለው ድጋፍ እንዳካተተም ጠቁመዋል። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም