የጽንፈኝነት መንስኤ የሆኑ ተቃርኖዎችን በማስታረቅ የተሻለች ኢትዮጵያን በጋራ መገንባት ይገባል

116

ሰኔ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጽንፈኝነት መንስኤ የሆኑ ተቃርኖዎችን በማስታረቅ የተሻለች ኢትዮጵያን በጋራ መገንባት እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት አዘጋጅነት "ከጽንፎች መሐል ወርቃማውን አማካይ ፍለጋ" በሚል መነሻ ሃሳብ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።

የዛሬው መድረክ ጽንፈኝነትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በመንግሥት በኩል ስለሚወሰዱ እርምጃዎች ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን  የትናንትና የዛሬ ታሪካዊ ተቃርኖ እንዲሁም በእኔና በእኛ ፖለቲካ ሚዛን መጉደል ከጽንፈኝነት መንስኤዎች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም ለጽንፈኝነት በር የሚከፍቱ ተቃርኖዎችን አስታርቀን የነገ ኢትዮጵያን በጋራ መገንባት ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ አኳያ መንግሥት የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ገልጸው፤ ነገር ግን ተቃርኖዎችን የማስታረቁ ኃላፊነት ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

በተለይም ለጽንፍ መንስኤ የሆኑ ተቃርኖዎችን ሚዛን ለማስጠበቅና ለማስታረቅ ኪነ-ጥበብና ሚዲያ የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም በበኩላቸው፤ አገራዊ ለውጡ መባቻ ጽንፈኝነት አገርን የፈተነ አደጋ እንደነበር አስታውሰው፤ የለውጡ መንግሥት በወሰዳቸው እርምጃዎች አገርን  ከብተና መታደጉን ገልጸዋል።

አሁንም የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በኃይል መጫን የሚሹ አካላት በአካባቢው ሰላም እያደፈረሱ መሆኑን ገልጸው፤  ከዚህ አኳያ መንግሥት የሕዝብ ቀዳሚ ጥያቄ የሆነውን ሕግ የማስከበር እርምጃ እየወሰደ ነው ብለዋል።

በፖለቲካ፣ ርዕዮተ-ዓለም፣ በእሳቤና መሰል ጉዳዮች ላይ ለጽንፈኝነት መንስኤ የሚሆኑ ችግሮችን ከመሰረቱ በመቅረፍ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ብዝሃነትን በአግባቡ ማስተናገድ፣ የታሪክ አተያይ ችግሮችን ማስታረቅ፣ የሥራ-አጥነት ችግሮችን መፍታት እንዲሁም የሰብዓዊ መብት፣ ፍትሕና የልማት ጥያቄዎችን መመለስ እንደሚገባም እንዲሁ።

ነጻና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማት ሪፎርምን ማጎልበት እና የጸጥታና ሕግ ተቋማት በማጠናከር የአክራሪነት፣ ጽንፈኝነትና ሽብርተኝነት ችግሮች እንዳይከሰቱ መከላከል ላይ መንግሥት በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የብልጽግና ፓርቲን ወክለው የተገኙት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር  ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት የተዘራውን የጽንፈኝነት ፖለቲካ ባህል መለወጥ ያስፈልጋል ብለዋል።

ጽንፈኝነት መጠቀሚያ ከሚያደርጋቸው ጉዳዮች መካከል በብሔርና ሃይማኖት "ተገፍቻለሁ" የሚል  ብሶትን በመቀስቀስ  ግጭት፣ መፈናቀልና ሞት እንዲከሰት አድርጓል ብለዋል።

ከዚህ አኳያ ብልግጽና ፓርቲ ከጽንፍ የፖለቲካ ባህል ወደ ወርቃማ አማካይ አስተሳሰብ ሽግግር ማድረግ እንደሚገባ በጽኑ ያምናል፤ ይህንን እሳቤ ለማስፈን ይሰራል ነው ያሉት፡፡

ለኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነት ስጋት የሆኑ የጽንፈኝነት ተቃርኖዎችን በማስወገድ ሁላችንም አሸናፊ በሚያደርገው መንገድ ለመራመድ የባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግም ነው የውይይት ሃሳብ አቅራቢዎቹ የተናገሩት።

የአስተሳሰብ ዋልታ ረገጥነት እና ጽንፈኝነት ማንንም አሸናፊ የማያደርግ በመሆኑ ሁሉንም ዜጋ ወደ አሸናፊነት የሚመራ መንገድ መቀየስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን ማዳከም የሚሹ አካላት ሁሉ ዋና መጠቀሚያ የሚያደርጉት ጽንፈኝነትን እንደሆነ ገልጸው፤  ለጽንፈኝነት መንስኤ የሆኑ ችግሮችን በውይይትና በድርድር መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም