ኮሚሽኑ ሀገር በቀል እውቀቶችን በመጠቀም ለህዝቡ አጀንዳ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታወቀ

3

ሀዋሳ፤ ሰኔ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በየአካባቢው ባሉ ሃገር በቀል እውቀቶች ላይ ተመስርቶ ለህዝቡ አጀንዳ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ከሲዳማ ክልል ርእሰ መስተዳድርና ካቢኔ አባላት ጋር “ለምክክር መድረኩ እውን መሆን የክልል መንግስታት ድርሻ” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በሀዋሳ መክሯል፡፡

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እንዳሉት ኮሚሽኑ ባለፉት ሶስት ወራት የዝግጅት ምእራፍ ከአዋጁ አስፈላጊነት ጀምሮ በሌሎች ነጥቦች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል።

ፕሮፌሰር መስፍን ጨምረው ስራው ከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል የሚጀምር በመሆኑ ከክልሎች ጋር የሚደረገው አጋርነትና አደረጃጀት ስራውን በሚፈለገው ልክ ለማከናወን አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ አንፃር ኮሚሽኑ በሀገር በቀል እውቀቶች ላይ ተመስርቶ ለህዝቡ አጀንዳ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከህዝብ የተጣለበትን ሃላፊነት በተገቢው መንገድ እንዲወጣ የሲዳማ አባቶች የሽምግልና ስርዓት አጋዥ ሊሆን እንደሚችል እምነታቸውን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ምክንያታዊ፣ ገለልተኛና ከማንም ተጽእኖ ውጭ ሆኖ አጀንዳዎችን በጥልቀት ከታች ወደ ላይ የሚመለከት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ተገኝወርቅ ጌቱ ናቸው።

ኮሚሽኑ ለዴሞክራሲ መሰረት የሚጥል እውቀት መር ውይይት በማድረግ እንደ ሃገር ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው ሃገሪቱን ወደ አዲስ ምእራፍ ያሻግራል ተብሎ እምነት የተጣለበት የብሄራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ስራ እንዲሳካ ክልሉ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የክልሉ ህዝብ ሰላም ፈላጊ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ የሚፈለገውን ሃገራዊ እድገት ለማምጣት ሰላምን በሚያደፈርሱ ጉዳዮች ላይ መወያየት ጊዜ የሚሰጠው አለመሆኑን አስምረውበታል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የትምህርት ቢሮ ሃላፊው አቶ በየነ በራሳ በየአካባቢው ጫፍ የወጡ ጉዳዮችን መፍታት የምንችልባቸው መልካም እሴቶች ያሉን ህዝቦች ነን ሲሉ ገልጸዋል።

በሲዳማ “የአፊኒን” የግጭት አፈታትና የዳኝነት ስርዓት ለአብነት ጠቅሰው የነዚህ እሴቶች ባለቤት ሆነን በማያጣሉ ጉዳዮች በመጋጨት በርካታ የእድገትና የለውጥ እድሎችን አጨናግፈናል ብለዋል።

በቀጣይ ኮሚሽኑ ለሚሰራቸው ስራዎች አጋዥ የሆኑ ተግባራትን በተመለከተ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን ክልሉ በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ከስምምነት ተደርሷል።