የቡሬ- ጎመርና ቡሬ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የአስፓልት መንገድ ግንባታ እየተፋጠነ ነው

2

ቡሬ፤ ሰኔ 10/2014 (ኢዜአ)፡ የቡሬ- ጎመርና ቡሬ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የ43 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ግንባታ ከ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በሚበልጥ ወጭ እየተፋጠነ መሆኑን የመንገድ ሥራው አማካሪ ድርጅት አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ በመንገድ መሰረተ ልማት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን አብራርተዋል።

ከለውጡ በፊት በመገዶች አስተዳደር የተሰሩ የአስፋልት ኮንክሪት መንገዶች 13 ሺህ ኪሎ ሜትር ያህል መሆናቸውን አስታውሰው፤ ከለውጡ በኋላ ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት በመንገዶች አስተዳደር በሀገር ደረጃ 4 ሺህ 700 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ኮንክሪት መንገዶች መገንበታቸውን አመልክተዋል።

በሀገራዊ ለውጡ በመንገድ ዘርፍ ተጠቃሚ ከሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች ውስጥ የምዕራብ ጎጃም ዞን አንዱ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዞኑ ባለፉት ሶስት ዓመታት 504 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ከ504 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ውስጥም የቡሬ-ጎመርና ቡሬ ኢንዱስትሪያል ፓርክ   የ43 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታን በአብነት አንስተዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን እየተገነባ ያለውን የቡሬ- ጎመርና  ቡሬ ኢንዱስትሪያል ፓርክ  የአስፋልት መንገድ ግንባታን በአብነት አንስተውም ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

እየተገነባ ያለው የቡሬ- ጎመርና ቡሬ ኢንዱስትሪያል ፓርክ  የአስፋልት መንገድ በከተማ 21 ሜትር በገጠር ደግሞ 10 ሜትር ስፋት እንዳለው በአማካሪ ድርጅቱ የፕሮጀክት ተጠሪ መሀንዲስ ኢንጅነር ዘገየ ጠና ለኢዜአ ገልጸዋል።

የአስፋልት መንገድ ሥራውን በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ ከተቋራጩና ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ኢንጅነር ዘገየ እንዳሉት መንገዱ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ በተሽከርካሪ ከሁለት ሰዓት በላይ የሚወስደውን ጉዞ ወደ 45 ደቂቃ ዝቅ ያደርገዋል።

በስራ ተቋራጩ የሜድሮክ ኮንስትራክሽን የቡሬ- ጎመር ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ሰምረዲን አዳነ በበኩላቸው የመንገድ ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን የወንበርማ ወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስማረ መኮንን በበኩላቸው መንግስት የህብረተሰቡን የዓመታት የመንገድ ጥያቄ ከግምት ውስጥ በማስገባት የወረዳውን ህዝብ ጥያቄ እንዲመለስ ማድረጉን ገልጸዋል።

አካባቢው የአየሁና የዚገም የእርሻ ልማት መገኛ መሆኑን ጠቁመው፤ መንገዱ  በወረዳው በጀትና በባለሀብቶች ተደጋጋሚ ጥገናዎች ቢደረጉለትም ዘላቂ መፍትሄ አለማስገኘቱን ተናግረዋል።

መንገዱ የሚያልፍበትን ቦታ ከ3ኛ ወገን ነፃ በማድረግ መንገዱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አይ ኤም ኤስ በተባለው አማካሪ ድርጅት ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው የቡሬ- ጎመርና ቡሬ ኢንዱስትሪያል ፓርክ  የ43 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ግንባታ  ወጭው በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን መሆኑ ተመላክቷል።

የአካባቢው ነዋሪዎች የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ ያመረቱትን ምርት  በቀላሉ ወደ  ገበያ አቅርቦ በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚ  መሆን እንዳልቻሉ ጠቁመዋል።

የአስፋልት መንገድ ግንባታ ስራው በመጀመሩ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፤ የመንገድ ስራው ስኬታማ እንዲሆን አቅማቸው በሚፈቅደው ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።