ቋሚ ኮሚቴው በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሕግ በማስከበር ረገድ የተመዘገቡ ውጤቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳሰበ

74

ሰኔ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሕግ በማስከበር ረገድ የተመዘገቡ ውጤቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

በዞኑ በወንጀል ተጠርጥረው በሕግ ጥላ ሥር የሚገኙ ዜጎች ሰብዓዊ አያያዝ አበረታች መሆኑንም ቋሚ ኮሚቴው ጠቁሟል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የምክር ቤት አባላት በተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ የልማትና ሌሎች ተግባራት እንዲጎበኙ መጠየቃቸው ይታወሳል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥያቄ ተከትሎ  በምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሸዋ ዞን እየተካሄደ ያለውን የሕግ ማስከበር ሂደትና የተጠርጣሪዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ኢሳ ቦሩ እንዳሉት፤ በዞኑ ሕብረተሰቡን በማሳተፍ  ሰላም ለማስፈን እየተወሰደ ያለው እርምጃ  አበረታች ነው።

በዞኑ በተከናወኑ የሕግ ማስከበር ሥራዎች የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠል ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ላይ ትኩረት ተደርጎ እንዲሰራም አሳስበዋል፡፡

በተለይ የጸጥታ አካላት ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት አሸባሪው ሸኔ የዞኑን ሰላም እንዳያውክ የሚያከናውነውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ነው ያስገነዘቡት፡፡

በዞኑ እየተከናወነ ባለው ሕግ የማስከበር ሥራ በወንጀል ተጠርጥረው በሕግ ጥላ ሥር የሚገኙ ግለሰቦች ሰብዓዊ መብት አያያዝ  አበረታች መሆኑንም አንስተዋል።

የተጠርጣሪዎችን ሰብዓዊ መብት ከመጠበቅ ባሻገር በፍጥነት ፍትሕ እንዲያገኙ ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አባቡ ዋቆ በበኩላቸው፤ አሸባሪው ሸኔ በዞኑ በሚገኙ በርካታ ቀበሌዎች ሕዝቡ ተረጋግቶ የዕለት ተለት ተግባሩን እንዳይፈጽም  ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

በዚህም ቡድኑ ሰላማዊ ዜጎችን በመግደል፣ አርሶ አደሮችን በመዝረፍና በማሰቃየት ዓላማ-ቢስ ስብስብ መሆኑን በተግባር አሳይቷል ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡

ባለፉት ሁለት ወራት የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ ፌዴራል ፖሊስ እና የክልሉ ጸጥታ ኃይሎች በጥምረት ሕግ የማስከበር እርምጃ በመውሰድ የአካባቢውን ሰላም ማስጠበቃቸውን ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

በሕግ የማስከበር ሥራው ላይ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ጠቁመዋል።

ሕብረተሰቡ ከስጋት ወጥቶ ወደ ልማቱ እንዲያተኩር ሕግ የማስከበር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም