በህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት በህግ ቁጥጥር ስር ያሉ ዜጎች አያያዝ የተሻለ ነው

96

ሰኔ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) በህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት በህግ ቁጥጥር ስር ያሉ ዜጎች አያያዝ የተሻለ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለፀ።

የቋሚ ኮሚቴው ንኡስ አባላት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞንና አዳማ ከተማ በህግ ጥላ ስር ያሉ ዜጎች ያሉበትንና የአያያዝ ሁኔታ የመስክ ምልክታ አድርገዋል።

በምክር ቤቱ የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢሳ ቦሩ ለኢዜአ እንደገለጹት በህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት በአዳማና ምስራቅ ሸዋ ዞን በህግ ቁጥጥር ስር ያሉ ዜጎች አያያዝና ያሉበት ሁኔታ የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ወራት በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት ዜጎች እንዳይጎዱ ጥንቃቄ የተሞላበት መሆኑን መገንዘብ ችለናል ነው ያሉት።

በምስራቅ ሸዋ ዞን በ42 ቀበሌዎች ላይ ሸኔ ሲንቀሳቀስ እንደነበርና አሁን ሙሉ በሙሉ በሚባልበት ደረጃ 38 ቀበሌዎች ከአሸባሪው ቡድን ነፃ ማውጣት መቻሉን ተገንዝበናል ብለዋል።

ነገር ግን ዜጎች ከስጋት ነፃ የሚሆኑበት አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ከማድረግ አንፃር ሰፊ ስራ መስራት እንደሚገባ በየደረጃው ካሉት የፀጥታና አስተዳደር አካላት፣ከህዝብ ተወካዮች ጋር ተወያይተን ከመግባባት ደርሰናል ብለዋል።

ከቦታ ጥበት በስተቀር ምንም አይነት ጫና እንደሌለ በህግ ቁጥጥር ስር ካሉት አንደበት መረዳት መቻላቸውና ይሄም ጥሩ መሻሻል መሆኑ ምክትል ሰብሳቢው ገልፀዋል።

በተለይ ከቤተሰብ ርቆ በጊዜያዊ ማቆያ ፖሊስ ጣቢያ ያሉት ተጠርጣሪዎች ተገቢውን የማጣራት ስራ በመስራት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መወያየታቸውን አንስተዋል፡፡

በመስክ ምልከታው በህግ ማስከበሩ ሂደት ህብረተሰቡ ደስተኛ መሆኑን ታዝበናል ያሉት ደግሞ የኮሚቴው አባል አቶ አዳነ ማንዴ በበኩላቸው የሽብር ቡድኑ ሸኔ በዋናነት የሚንቀሳቀስበትን ቦሰት ወረዳና ዎለንጭት ከተማ ድረስ የመስክ ምልከታ አድርገናል ብለዋል።

በዚህም ህብረተሰቡ መንግስት እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር ዘመቻ አጠናክሮ እንዲቀጥልና ህዝቡ ደስተኛ መሆኑን የተረደንበት ነው ብለዋል።ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም