የጸጥታ ተቋማት ህግን አክብረው ተልዕኳቸውን በብቃት የመፈጸም አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ሙያዊ ድጋፍን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

1

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጸጥታ ተቋማት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግጋትን አክብረው ተልዕኳቸውን በብቃት የመፈጸም አቅማቸውን ለማጎልበት ሙያዊ ድጋፍን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ፍቃዱ ፀጋ ተናገሩ፡፡

የሚኒስትሮች ግብረ-ኃይል ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመሆን ለክልል የጸጥታ አካላት  የዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ እና የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግ ዙሪያ ሥልጠና መስጠት ተጀምሯል፡፡

ሥልጠናው ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮችና የፍትሕ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

በሥልጠናው ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ የተገኙት የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ፍቃዱ ፀጋ፤ የሥልጠናው ዋነኛ ዓላማ የጸጥታ አካላት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕጎችን ባከበረ መልኩ የሚሰጣቸውን ተልዕኮ እንዲወጡ ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪ ሥልጠናው የጸጥታ አካላት ሰላማዊ ዜጎችን እንዴት መጠበቅና መደገፍ እንዳለባቸው ግንዛቤ የሚሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕጎች መከበር የጸጥታ ተቋማትን ተዓማኒነትን ከማሳደግ በላይ ሰላምን ለማስፈን እንደሚረዳም ጠቁመዋል፡፡  

የጸጥታ ተቋማት የሰብዓዊ መብት ሕጎችን ባከበረ መልኩ ተልዕኳቸውን በብቃት የመፈጸም አቅማቸውን ለማጎልበት ሙያዊ ድጋፍን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

በተቋማቱ የሚሰሩ አካላት በስልጠና አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ እየተደረገ ስለመሆኑም ለአብነት አንስተዋል፡፡

ይህም ተዓማኒና በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚያበረክተው ባሻገር በዓለም አቀፍ በተደነገጉት የሰብዓዊ መብት ሕጎች መከበር ጠንካራና ተዓማኒ ተቋማዊ አሰራርን በማጎልበት የተረጋጋች አገር ለመገንባት ያግዛል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተቀባይነት ይበልጥ ለማሻሻል እንደሚያግዝም እንዲሁ፡፡

በዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የኮሙኒኬሽን የሥራ ክፍል ምክትል ኃላፊ ዘውዱ አያሌው በበኩላቸው፤ በግጭት ምክንያት ጉዳት ለሚደርስባቸው ወገኖች መብታቸው እንዲከበር ለማድረግ ዓለም አቀፍ ሕጎችን መረዳት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

ሊደርሱ የሚችሉ የመብት ጥሰቶችን ከመከላከል አንጻርም የተሻለ ግንዛቤ የሚፈጥር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡       

በሥልጠናው በመሳተፍ ላይ የሚገኙት የጸጥታ አካላት በሰጡት አስተያየትም ሕጎቹን ማወቅና መረዳት ሥራዎቻቸውን በብቃት እንዲወጡ እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪ ስልጠናው በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ በማድረግ ረገድ በምን መልኩ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ግንዛቤ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡