ዘርፉን ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሻገር የሚያስችል የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ እየተዘጋጀ ነው

102

ሰኔ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሻገር የሚያስችል ረቂቅ የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊስ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ተናገሩ፡፡

ረቂቅ ፖሊሲውን ለማዳበር የሚያስችል የሁሉም ክልሎች ምክትል ርዕሰ መስተዳደሮችን ጨምሮ የሁለቱ ከተማ መስተዳድር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዘርፉ ቋሚ ኮሚቴ አባላትና አመራሮች የተሳተፉበት መድረክ በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የመድረኩ አላማ ፖሊሲውን ለማዳበር ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በአፈፃፀምና የህግ ማእቀፍ ዝግጅት ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑና የራሳቸውን አስታዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማስቻል ነው ተብሏል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት አዲሱ ረቅቅ የኢንዲስትሪ ልማት ፖሊሲ ዓለም አቀፍ አማካሪዎችንና የሀገር ውስጥ ምሁራንን አካቶ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ሲዘጋጅ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ነባሩ የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ ሰፊ ክፍተት የነበረበት ነው ያሉት ሚኒስትሩ በተለይ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ በሀገር ልማት ውስጥ የሚጠበቅበት ሚና እንዳይኖረው ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ሚንስትሩ ጨምረው እንዳሉትም ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርት እንዲተኩ ትኩረት ያልሰጠና የሴክተሩ ልማት የተፈለገውን ያህል እንዳይራመድ ያደረገ ነው፡፡

አዲሱ ረቅቅ ፖሊሲ የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ልማት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሻገር የሚያስችል ከመሆኑም ባሻገር የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማሳካት ቁልፍ ሚና የሚኖረው ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስቱሪውን የቀጣይ 10 ዓመታት የአፈፃፀም አቅጣጫዎች የዳሰሰ ነው ያሉት አቶ መላኩ የተቀናጀ ና ወጥነት ያለው ትግበራ እንዲኖረው ክልሎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ግልፅ የህግ ማእቀፎችን ያከተተ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶችን አቅናጅቶ በዘርፉ ልማት ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እንዲሁም የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን ለማበረታታትና ለመደገፍ ግልፅ አቅጣጫዎችና አማራጮችን የዳሰሰ መሆኑን አቶ መላኩ ተናግረዋል።

በዚህም "ኢትዮጵያ ታምርት" የሚለውን መርህ ለማሳካት ቁልፍ መሳሪያ የሆነ ረቂቅ ፖሊሲ መሆኑን ገልፀው ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ በአፈፃፀም ወቅት ልዩነት እንዳይኖርና የተቀናጀ ርብርብ ለማድረግ ጭምር ሁሉም ግልፅ ግንዛቤ እንዲኖረው ነው ብለዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የኢንዲስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር አማረች ባክሎ በበኩላቸው አሁን ያለው የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ ለረዥም ጊዜ የቆየና ሀገሪቱ ከደረሰችበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ ባለመሆኑ አዲስ ረቅቅ ፖሊሲ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡

ግብርናን ተንተርሶ ያለውን የሀገሩቱን ኢኮኖሚ በኢንዱስትሪ መር ለመተካት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብና ቁርጠኝነት ይጠይቃል ብለዋል።

የረቅቅ ፖሊስው ላይ ያተኮረ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ያለው መድረክ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም