የሰራዊቱን ስም ማጉደፍ የሀገርን ክብር ዝቅ ማድረግ በመሆኑ ተገቢነት የለውም-የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች

2

ጎንደር፤ ሰኔ 10/2014 (ኢዜአ)፡ ለሀገርና ህዝብ መስዋዕትነት እየከፈለ ያለን የመከላከያ ሠራዊት ስም ማጉደፍ የሀገርን ክብር ዝቅ ማድረግ በመሆኑ ተገቢነት የለውም ሲሉ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ አንዳንድ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰጡት ማብራሪያና ምላሽ ወቅታዊ ትክክለኛና ግልጸኝነትን የፈጠረ መሆኑ ተመላክቷል።

በጎንደር ከተማ የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ አድማስ ደሞዜ ለኢዜአ እንደገለጹት ሀገር እንዳትፈርስ ውድ ህይወቱን መስዋዕት እያደረገ ለሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት አክብሮትና አድናቆት አላቸው፡፡

ቡድኖችና ግለሰቦች የማህበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀም ከህዝብ አብራክ የወጣን ሠራዊት ስሙን እንዲያጎድፉ መፈቀድ እንደሌለበት ተናግረዋል።

የሠራዊቱን ስም ባልተገባ መንገድ እያነሱ ባሉ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ አመልክተው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት ጥብቅ መልእክትም ሳይሸራረፍ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።

”መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር የወሰደው እርምጃ በከተማችን አስተማማኝ ሰላም ያሰፈነ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥል” ብለዋል።

የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም መንግስት እየወሰደ ያለው የኢኮኖሚ እርምጃ መጠናከር እንዳለበት ጠቅሰው፤ በተግባር የድሃውን የኑሮ ጫና ማቃለል እንዲችል መሬት ላይ ያለው አሰራር ሊፈተሽ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ሌላው የጎንደር ከተማ ነዋሪ አቶ ፍትጉ አዳነ በበኩላቸው ”ሠራዊት የሌለው ሀገርና ህዝብ ህልውናና ሉአላዊነቱ መቼም ቢሆን የተረጋገጠ ባለመሆኑ ለመከላከያ ሠራዊታችንና ለሌችም የፀጥታ አካላት ትልቅ ክብር አለኝ” ብለዋል።

የህዝብ ልጅና መከታ የሆነውን የመከላከያ ሠራዊት ክብር ዝቅ ለማድረግ የሚሹ አካላት የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት የማይፈልጉ የውጪ ሃይሎች ተባባሪ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሠራዊቱን  ታላቅነት ዝቅ በማድረግ የሚሰነዘር ማናቸውም ሀሳብና ተግባር  የሚወገዝ መሆኑን አመልክትው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ መተግበር ይገባዋል ብለዋል።

መንግሰት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት እንዲሁም የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠይቀዋል።

በምግብ እራስን ለመቻል ለሚደረገው ጥረት አጋዥ የሆነው የበጋ ስንዴ ልማትም ተስፋ ሰጭ መሆኑን ጠቅሰው፤ የልማት ሥራው በተቀናጀ አግባብ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት እንቅስቃሴ እንደሆነ አመልክተዋል።

”ስንፍናና ታካችነት ለድህነት የዳረጉን ጎጂ ባህሎች ናቸው” ያሉት ነዋሪው፤ የጓሮ አትክልት ልማት ስራውን በመደገፍ በመኖሪያ ቤታቸው እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል።

”የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ በህዝቡ ውስጥ የነበረውን ብዥታና አሉባልታዎች ማጥራት ያስቻለ ነው” ያሉት ደግሞ የማራኪ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ቢሰጥ መኳንንት ናቸው፡፡

የህግ ማስከበር ሥራው በሚኖሩበት ክፍለ ከተማ ዝርፊያ፣ ግድያና የሰው ማገት ወንጀልን ማስቆም መቻሉን አመልክተው፤ ይህም በሰላም ወጥቶ ለመግባት የሚያስችል ምቹ የሰላም ድባብ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

መከላከያ ሠራዊት የሀገር ምሰሶና ጠባቂ በመሆኑ ስሙን በከንቱ የሚያጎደፉ አሉባልተኞች ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ጠቁመው፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልእክትም እንደሚደግፉት ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፋኖ አባላት የሰጡት እውቅና እንዳስደሰታቸው ጠቁመው፤ ይህም መንግስት በህግ ማስከበር ሽፋን ፋኖን እያሳደደ ነው የሚለውን አሉባልታ ያከሸፈ ነው ብለዋል፡፡