''ዲንካ'' እና- የባለሙያዎቹ ስጋት

440

''ዲንካ'' እና- የባለሙያዎቹ ስጋት

(በቀደሰ ተክሌ-ሚዛን አማን)

 ለሙዚቃው ዓለም ግዕዝ፣ ዕዝልና አራራዩን ለዓለም ያበረከተች ተዝቆ የማያልቅ ሀገርኛ ሀብት፣ እውቀትና ጥበብ ምንጭና አውድማ ናት፤  ከበሮና አታሞ፣ ነጋሪት እምቢልታ፣ በገና መሰንቆ፣ ክራርና ዋሽንት ከሌሎች ያልተዋሰቻቸው በራሷ ከራሷ አዘጋጅታ ለሙዚቃም ሆነ ለዝማሬ ማጀቢያ የምትጠቀም ባለፀጋና ኩሩ ሀገር ነች- ኢትዮጵያ።

አምባሰል፣ትዝታ፣ አንቺ ሆዬና ባቲ ቅኝቶቿ፣ ያሬዳዊ ዜማና ዝማሬስ ቢሆን ምንጫቸው የት ሆነና። በእቅፏ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች እንደ ወጋቸው የሚጠቀሟቸው ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎችም ልዩ ናቸው።

ከተለያዩ የተፈጥሮ ውጤቶችና የእንስሳት ቀንድ የሚዘጋጁ የትንፋሽ መሳሪያዎች የሚሰጡት ውብ ድምጽ በጆሮ ለመስማት ያጓጓል።ከባህላዊ የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪዎች አንዱ ነው ''ዲንካ''።  ረጅሙ የትንፋሽ መሳሪያ እንደሆነ የሚነገርለት ዲንካ ትውልድና እድገቱ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን ነው።

አቶ ታምራት ተክሌ ይባላሉ። የዲንካ ባለሙያና ተጫዋች ናቸው። ባለሙያው እንደሚሉት ዲንካ  ከትላልቅ በዓላት፣ ከንጉስና ባላባቶች ሞት ውጭ በማንኛውም ጊዜ ለአገልግሎት አይውልም። የዳውሮ ልዩ መገለጫ የሆነው ዲንካ ሰባት ቅኝቶች ሲኖሩት በለቅሶና ደስታ ጊዜ ቅኝቶቹም ተለይተው ጥቅም ላይ ይውላሉ።

የዲንካ ተጫዋቾች ያላቸውን ተፈጥሯዊ የቅኝት ልየታ እውቀት በመጠቀም የተለያየ ድምጽ ያወጣሉ። ሰባቱ የቅኝት ድምጾችም  ሰባት አይነት ስያሜ ሲኖራቸው "ኮናሽያ፣ ካርቺያ፣ የዳ፣ ጋድሊያ፣ ሎማቷ፣ ታታ እና ሀታ" የስያሜዎች መጠሪያ ነው።

ሰባቱ የቅኝት ድምጾች የተለያየ ድምጽ ሲያወጡ ድምጾቹን ተከትሎ "ዳርቢያ" ወይም ከበሮ ይመታል። "ዲንካቶ" የሚባል ጨዋታ በውዝዋዜ ይደምቃል። የዲንካቶ ጨዋታን ውዝዋዜ በበላይነት የሚቆጣጠረው ዲንካ ነው። በዲንካቶ ጨዋታ የተመልካችን አይን የሚዘው ትልቁ ሚስጢር የዲንካና ከበሮ ውህደት የተጫዋቾችን ውዝዋዜ በጥዑም ምት ማንጸባረቁ ነው።

እንደ አቶ ታምራት ገለጻ ዲንካ ዘመናዊ ነገር ያልታከለበት ባህላዊ የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያ ሲሆን  ከቀርቀሃ ይዘጋጃል። ቁመቱ ከሦስት ሜትር እስከ አራት ሜትር እርዝማኔ አለው።የቀርቀሃ አንጓን የዳውሮ ጠቢባን እጆች ብረት በእሳት አግለው ይቦረቡሩታል። ቀርቀሃው ወጥ የሆነ ክፍተት ሲኖረው ጫፉ ላይ የአጋዘን ቀንድ ይደረግበታል። የዲንካ ድምጽ ጎልቶ እንዲወጣ የበሬ ቀንድ ሰፋ ተደርጎ እንደ ዋንጫ በመዘጋጀት በላይኛው የመጨረሻ ጫፍ ላይ ይታሰራል። ለመሣሪያው ድምቀትና ውበትም የፍየል ቆዳ ተዘልዝሎ በዲንካ ጫፍ ላይ ከቀንዱ በታች እንደ ከረባት ተደርጎ ይንጠለጠላል።

በሕብረት መጫወት ዲንካን ከሌሎች የትንፋሽ መሳሪያዎች የተለየ ባህርይ እንዲኖረው አድርጎታል።ቁጥራቸው አምስት ሲሆን እያንዳንዳቸው ''ዞሃ፣ ሔሲያ፣ ማራ፣ አይትያና ላሚያ'' ይባላሉ። ነገር ግን ''ዞሃ'' በቁመት ከሁሉም  የሚረዝም ነው።  ዲንካን ከተጠቀሱት ቁጥሮች አንዱ ከጎደለ አይያዝም።

ጥበበኞቹ የዳውሮ የዲንካታ አዋቂዎች አንዱን ዲንካ በከበሮ ተከትው ይጫወታሉ። "የዲንካቶ ከጫ" ባንድ በአራት ዲንካ፣ በአንድ ከበሮ፣ በሁለት ጦር እና አራት ተወዛዋዥ ሴቶች የተጣመረ ነው። ከእነዚህ አንዱ ቢጎድል ዲንካ አገልግሎት አይሰጥም። አንዷን ዲንካ ለብቻ ፎቶ ለማንሳት እንኳ ባለሙያዎቹ አይፈቅዱም። ይህ የባህል ጥበቃ እጅግ የሚያስገርም ሆኖ ከቦታው መመልከት ችለናል።

የተተኪ መጥፋት የዲንካቶ ተጫዋቾችና ባለሙያዎች ስጋት ነው። ለአብነት አሁን ላይ አገልግሎት መስጠት ያቆመውን ''ዞሃ'' መጫወት የሚችል ሰው የለም። አሁን ካለው የዲንካቶ ባንድ አንዱ ቢታመም ጨዋታው ይቀራል እንጂ ተተክቶ ገብቶ የሚጫወት እንደሌለ አቶ ታምራት ይናገራሉ። ''በእጅ ያለ ወርቅ እንደ መዳብ ተቆጥሮ ትልቅ የሀገር ሀብትና ቅርስ ተጠቃሚ አላገኝም'' ብለዋል።

ሙያው በጽሑፍ የሚገኝ ሳይሆን ድምጽ አዳምጦ በአዕምሮ ውስጥ በማመላለስ የሚያዝ በመሆኑ ወጣቶችን አሁን ካልተካን ከቅድመ አያቶቻችን የተረከብነው ባህላዊ ጥበብ መቋረጡ ነውና የሚመለከተው አካል ትኩረት ሊያደርግ ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል።

ሌላው የመሣሪያው ተጫዋች አቶ በየነ አችሌ እንደሚሉት ዲንካን ለመጫወት በብሔረሰቡ የተቀመጠ የዕድሜ ገደብ አለ።  ዕድሜው አሥራ ሁለት ዓመት ያልሞላው ከዲንካ አጠገብ ዝር እንዲል አይፈቀድም። ይህም ለመሣርያው ክብርና ይዘት መጠበቅ ታስቦ ነው ብለዋል።

በአዕምሮ በማሰላሰል የሚገኝና ብዙ ትንፋሽ የሚጠይቅ በመሆኑ ትክክለኛውን የዲንካ ድምጽ ለማውጣት በሳል መሆንን ይጠይቃል። ዲንካን ለመልመድ እንደ ግለሰቡ አቀባበልና ትኩረት ከአንድ ዓመት እስከ አራት ዓመት ሊፈጅ እንደሚችል ይናገራሉ።

የዳውሮ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳዕሞ ደስታ እንዳሉት ዲንካ ከማህበረሰቡ ተፈጥሮ አብሮት ያደገ ሲሆን በመኻል መቀዛቀዝ ታይቶበታል።የተጠቃሚ ቁጥር ቀንሶ ለመጥፋት ተቃርቦ እንደነበር አስታውሰው፤የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በመስራት ዲንካን  በማንኛውም መርሐ ግብር ላይ ጥቅም ላይ እንዲውል የማበረታታት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪ በወረዳ ደረጃ የዲንካታን ባንድ በማዋቀር እንዲለማመዱ እያደረጉ መሆናቸውን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል። እስካሁን በዞኑ ከሚገኙ አስር ወረዳዎች ውስጥ ስምንቱ የዲንካ ባንድ አደራጅተዋል። ይበልጥ በማስተዋወቅ ሀገራዊ ሀብትነቱን ለማጉላት በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

በየማህበረሰቡ ተደብቀው ለመጥፋት የተቃረቡ እንደ ''ዲንካ'' ያሉ ኢትዮጵያዊ የትንፋሽ መሳሪያዎች እንዳሉ ይታመናል። ባህላዊና ኢትዮጵያዊ የሆኑ የሙዚቃ መሳሪያዎችን በጥንቃቄ በማዘመን አልያም እንደነበሩ መገልገልና ተገቢውን ትኩረትና ክብር መስጠት ይገባል። ኢትዮጵያን መውደድ ያላትን ነገር በማክበር ይገለጣል።ኢትዮጵያን መስለን ኢትዮጵያን ሁነን በመኖር ኢትዮጵያዊነታችንን እናለምልም።

ሰላም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም