የተፈጥሮ ሀብቶችን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማጉላት በትኩረት መሰራት እንዳለበት ምሁራን አመለከቱ

300

ሚዛን፤ ሰኔ 10/2014 (ኢዜአ) የተፈጥሮ ሀብቶችን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማጉላት በትኩረት መሰራት እንዳለበት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ተናገሩ።

በዩኒቨርስቲው የሥነ ህይወት ትምህርት ክፍል መምህር አንዷለም አዲሞ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ እያከናወነች ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከራሷ አልፎ ለቀጠናው ሀገሮች ውጤት የሚያስገኝ ነው።

የአየር ንብረት ለውጥና የአፈር መሸርሸርን ከመጠበቅ በላይ፤ ለግብርና ሥራ ውጤታማነት የሚኖረው አዎንታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

''የትኛውንም ያክል ኢኮኖሚ ቢያድግ የብዝሃ ህይዎት ጥበቃ የተጠናከረ ካልሆነ ዕድገት ሊመዘገብ አይችልም'' ብለዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚተከሉ ችግኞች በአግባቡ ከተያዙ የአፈር ለምነትን ከማምጣት፣ የተፈጥሮ ሚዛንን ከመጠበቅና መሬት እንዳይሸረሸር ከማድረግ በተጨማሪ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የሚተከሉት ችግኞች ሲያድጉ ለንብ ማነብ ሥራ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ጀምሮ ፍሬያቸውን ለምግብነትና ለገበያ በማቅረብ መጠቀም እንደሚቻል ጠቅሰዋል።

ሁሉም ሰው የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅና በማልማት የኑሮ ዘይቤውን የተስተካከለ ማድረግ እንደሚችል አመልክተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ረዳት ፕሮፈሰር ጥምቀቴ ዓለሜ በበኩላቸው ተፈጥሮን በአግባቡ ተንከባክቦ መያዝ ከተቻለ ለግብርና ምርትና ምርታማነት ፋይዳው የጎላ ነው።

በምርት እጥረትና ፍላጎት መብዛት ሀገራችን ውስጥ የተከሰተው የኑሮ ውድነት ሚዛኑን እንዲጠብቅ "አረንጓዴ ሀብቶቻችንን በማልማት ወደ ኢኮኖሚ መቀየር መቻል አለብን" ብለዋል።

አረንጓዴ አሻራው ለግብርናው ዘርፍ የሚያስገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ታሳቢ በማድረግ በችግኝ ተከላ ወቅት ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸውን ችግኞች መትከል ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በርካታ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ቢሆንም፤ ሀብቱን ወደ ኢኮኖሚ ከመቀየር አኳያ ያለው ክፍተት ተገቢውን ጥቅም ሳታገኝ እንድትቆይ ምክንያት መሆኑን አመልክተዋለ።

''እንደ ሀገር ክፍተቱን በመሙላት ባለን ሀብት ለማደግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታን መፍጠር ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ'' ነው ብለዋል።

ከደን ሊገኝ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ሀብት በጥናትና ምርምር አስደግፎ መጠቀም ከተቻለ፤ ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ዕድገት የምታስተናግድ ሀብታም ሀገር መሆን እንደምትችል ጠቅሰዋል።

አርሶ አደሮች በማሳቸው የፍራፍሬ ችግኞችን በብዛት በመትከል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ረዳት ፕሮፈሰር ጥምቀቴ መክረዋል።

ምሁራኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ ለማድረግና የተፈጥሮ ሚዛን ተጠብቆ ተገቢውን ዝናብ ለማግኘት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በቀጣዩ ሳምንት እንደሚጀመር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማሳወቃቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም