የ2014/2015 ምርት ዘመን የክልሉ የመኸር ተግባራት የንቅናቄ መድረክ በሚዛን አማን እየተካሄደ ነው

127

ሚዛን ሰኔ 10/2014 (ኢዜአ)…በክልሉ ዘመናዊ የእርሻ ልማት በማስፋፋት ምርታማነትን ለማሳደግ ይሰራል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር - ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አስታወቁ።

በክልሉ ግብርና ቢሮ አዘጋጅነት የ2014/2015 ምርት ዘመን የግብርና ሜካናይዜሽንና የመኸር ግብርና ተግባራት የባለድርሻ አካላት የንቅናቄ መድረክ በሚዛን አማን እየተካሄደ ነው።

በንቅናቄ መድረኩ  ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር - ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እንዳሉት ክልሉ ለግብርና ልማት ሊውል የሚችል ሰፊ ለም መሬት አለው።

ባለፈው የምርት ዘመን በተለያዩ ሰብሎች ከለማው 297 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡንም አስታውሰዋል።

የተገኘው ምርት ክልሉ ካለው ተስማሚ መልክዓ ምድርና አየር ንብረት አንጻር "አፈጻጸሙ አነስተኛ ነው" ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በ2014/015 የምርት ዘመን ልማቱን ወደ 350 ሺህ ሄክታር ለማስፋት ይሰራል ብለዋል።

ከዚሁ የግብርና ልማትም ከ14 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን እንዲሁ።

ምርታማነትን ለማሻሻል ትራክተሮችን በግዥና በኪራይ ለአርሶ አደሩ በማቅረብና የኩታ ገጠም ልማትን ለማስፋፋት ጥረት እንደሚደረግ አመላክተዋል።

በዚህ ረገድ ከፌደራል መንግስት ጋር በመናበብ የግብዓትና ምርጥ ዘር አቅርቦትን ለማሻሻል እንደሚሰራና ለዘመናዊና ባህላዊ መስኖ ልማት መጠናከርም ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው ክልሉ ለዘመናዊ ግብርና ልማት እምቅ አቅም ቢኖረውም በተለያዩ ተግዳሮቶች የሚፈለገውን እመርታ ማስመዝገብ አልተቻለም።

ለልማቱ ማነቆ የሆኑትን በመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫ ከማስቀመጥ ባለፈ የሜካናይዜሽን ልማትን ተግባራዊ በማድረግ በመጪው ምርት ዘመን ከምግብ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ የሚቀርብ ምርት ለማምረት ርብርብ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

የግብርና ቴክኖሎጂን ደረጃ በደረጃ በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በማሳደግ ሀገራዊ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘው ውጥን እንዲሳካ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።

እንደ አቶ ማስረሻ ገለጻ ክልሉ ከሰብል እርሻ በተጨማሪ ለፍራፍሬና እንስሳት ሀብት ልማት ያለውን ተስማሚነት ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየር የንቅናቄው ሥራ አስከ አርሶ አደሩ ድረስ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው በዚሁ የንቅናቄ መድረክ ላይ ከፌዴራል፣ ከክልሉ፣ ከዞንና ወረዳ የተውጣጡ የዘርፉ የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

በቆይታቸውም የ2013/14 የግብርና አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ እንደሚገመገምና በቀጣይ ዓመት እቅድ ላይ በመወያየት አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም