ታጠቅ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከሚያስፈልገው የድንጋይ ከሰል ግብዓት 80 በመቶውን ከአገር ውስጥ በመጠቀም ገበያን ለማረጋጋት እየሰራ መሆኑን ገለጸ

165

ሰኔ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ማስፋፊያ አካል የሆነው ታጠቅ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከሚያስፈልገው የድንጋይ ከሰል ግብዓት ወስጥ 80 በመቶውን ከአገር ውስጥ በመጠቀም ገበያን ለማረጋጋት እየሰራ መሆኑን ገለጸ፡፡

ፋብሪካው አሁን ላይ በቀን እስከ 20 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶን ለገበያ እያቀረበ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ማስፋፊያ አካል የሆነው የታጠቅ ሲሚንቶ ፋብሪካ  በ50 ሚሊዮን ዶላር የተቋቋመ ሲሆን የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ከሚያመርተው  ምርት 40 በመቶውን ይሸፍናል።

በኬሚካልና ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ የታጠቅ ምርትና ኢንጅነሪግ መምሪያ ተጠባባቂ ኃላፊ አቶ ዳንኤል አጥላው ፋብሪካው በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ላሉ ከተሞች ምርት እንዲያቀርብ  ታልሞ መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡

በፋብሪካው የሚመረተው ሲሚንቶ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ያሟላና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ መሆኑንም አመላክተዋል።

ሲሚንቶን በማምረት ሂደት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ወጪ ለድንጋይ ከሰል ግዥ የሚወጣ በመሆኑ ለምርት አለማደግ ተግዳሮት መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ፋብሪካ ከሚያስፈልገው የድንጋይ ከሰል ግብዓት ውስጥ 80 በመቶውን ከአገር ውስጥ በመጠቀም ገበያን ለማረጋጋት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የድንጋይ ከሰል ፍላጎቱን በአገር ውስጥ ምርት ለማሟላት እንደሚሰራም ነው የጠቆሙት፡፡

ይህም ለድንጋይ ከሰል የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ከማስቀረት ባሻገር የሲሚንቶ ምርትን ለማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅትም ፋብሪካው በቀን 20 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ በማምረት ለገበያ እያቀረበ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡

የጥሬ እቃ ግብዓት፣ የመለዋወጫ እቃዎችና የኃይል አቅርቦት ችግር በፋብሪካው ስራ ላይ ተግዳሮት እየፈጠረ መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡

እነዚህና መሰል ችግሮች ከተፈቱለት ፋብሪካው በአጭር ግዜ ውስጥ ምርቱን በእጥፍ በማሳደግ የአገሪቱን የሲሚንቶ ፍላጎት ለማሟላት የበኩሉን ሚና እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።   

የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሲሚንቶ ፍላጎት ከ11 ሚሊዮን ቶን በላይ ቢሆንም አሁን ላይ ሁሉም ፋብሪካዎች የሚያመርቱት ከስምንት ሚሊዮን ቶን ያልበለጠ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም