ለአገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት ባህላዊ እሴቶችን መጠቀም ይገባል – የሀገር ሽማግሌዎች

2

ሶዶ ፤ ሰኔ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) ብሔራዊ የምክክር መድረኩ ስኬታማ እንዲሆን በማህበረሰቡ የቆዩ ባህላዊ እሴቶችን መጠቀም እንደሚገባ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።

ኢትዮጵያ ህዝቦቿን በፍቅርና በአብሮነት ይዛ ለመጪው ትውልድ የተመቸ ሀገር ሆና ለመቀጠል የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አገራዊ ምክክር ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየሰራች ትገኛለች።

የዘርፈ ብዙ ባህልና እምነት ባለቤት የሆነችው አገር በርካታ የቆዩና ማህበረሰቡ ሲገለገሉባቸው የቆዩ የነበሩ ማህበራዊ እሴቶች እንዳሏት እሙን ነው።

እነዚህን ባህላዊ እሴቶች ለአገራዊ ምክክሩ መጠቀም ደግሞ የምክክር መድረኩን ስኬታማ ለማድረግ እንደሚያስችል ኢዜአ ያነጋገራቸው የአገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ።

የሀገር ሽማግሌዎቹ ለኢዜአ እንደገለፁት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የቆዩ ተሞክሮዎቻቸውን በመጠቀም ለሀገር አንድነትና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ሊረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የስልጤ የሀገር ሽማግሌ ሀጂ መሐመድ ከሊል በየማህበረሰቡ ውስጥ ቅራኔዎችን በመፍታት ወደ ህግ ሳይቀርብ መግባባትና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የሚረዱ ባህሎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

“ያንን የአባቶቻችንን ግጭቶችን በመፍታት እርቀ ሰላም የማውረድ ባህላዊ እሴት በመተዋችን እንደማህበረሰብ ጉዳት ደርሶብናል” ይላሉ ።

በመሆኑም ዘላቂ ሰላምና አንድነት ለማጠናከር ታስቦ የሚካሄደው ብሄራዊ ምክክሩ እነዚህን ትውፊቶችን መሰረት ማድረግ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።

አገራዊ ምክክሩ የሚፈጠሩ ግጭቶችና አለመግባባቶችን በአካታች ምክክር በመፍታትና ቁርሾዎችን በማጥራት ዘላቂ ሰላም ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም መድረኩ ውጤታማ እንዲሆን ካለፈው የእርቅ ማውረጃ ስነስርዓታችን ተሞክሮ በመውሰድ ምክክሩን ማሳካት እንደሚገባ ምክረ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

ሌላው የኮንሶ የሀገር ሽማግሌ አቶ ካፖሌ ጌዲሾ “ሀገር አቅዳ የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት የሚያስፈልገን በአንድነት መወያየትና መመካከር ነው” ብለዋል ።

መመካከርና መወያየት ላለመግባባት መነሻ የሆኑ ችግሮችን በጋራ መፍትሄ በማፈላለግ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት ብቸኛ መንገድ መሆኑን ገልጸው ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን በየብሄረሰቦች ሲገለገሉበት የኖሩት ነው ያሉት።

በሀገር ግንባታ በተለይ የወጣቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑን አመልክተው፤ ችግሮችን ከስር መሠረቱ ለመፍታት በውይይቱ ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

አያይዘውም “ባህላዊ እሴትና ወግ የሌለው ማህበረሰብ የለም” ያሉት አቶ ካፖሌ፤ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ባህላዊ እሴቶችን መሰረት ባደረገ መልኩ ሊከናወን እንደሚገባ ገልጸዋል ።

በተለይም በተለያየ መንገድ ተዛብቶ የተነገሩ ታሪኮችን ለማረም ባሉን ወጎችና ዕሴቶች ተጠቅመን በመወያየት እንፈታለን ለዚህ ሁሉም አበርክቶ ማሳረፍ አለበት ባይ ናቸው ።

የሀገር ሽማግሌ የትኛውንም ችግር የመፍታት አቅም እንዳለው ባህላችን ምስክር ነው ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ ባህላዊ ዕሴቶቻችንን ከዘመናዊ የህግ ዳኝነት ጋር በማዋሄድ የሚንመኘውን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ልንሰራ ይገባል ስሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።

በህዝቦች መካከል የግጭቶችና አለመግባባቶች ምክንያት እየሆነ የመጣውን ችግር በመፍታት የሀገር አንድነትና ሰላም ለማስጠበቅ ሀገራዊ ምክክሩን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ያስገነዘቡት ደግሞ የጎፋ የሀገር ሽማግሌ አቶ ማርቆስ ሳንኩራ ናቸው።

“ኢትዮጵያዊያን ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች ያሏቸው ህዝቦች በመሆናቸው የቀደመ የመከባበርና የአንድነት እሴቶችን በማጎልበት የሀገር ሰላምን ለማጠናከር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩሉን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል።

አገራዊ የምክክር መድረኩ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት የወጠነ በመሆኑ ከአባቶቻችን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የመወያየትና እርቀሰላም የማውረድ ባህላዊ እሴት መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አካታች ብሔራዊ ምክክር ለብሔራዊ መግባባታችን፣ ለዘላቂ ሰላማችንና ለአብሮነታችን በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት ከሰሞኑ በሶዶ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።