ኢንስቲትዩቱ በአፋር ክልል በጦርነት ለወደሙ ተቋማት መልሶ ማቋቋሚያ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ

165

ሰመራ፣ ሰኔ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአፋር ክልል አሸባሪው ህወሃት ከፍቶት በነበረው ጦርነት ለወደሙ ተቋማት መልሶ ማቋቋሚያ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን ያስረከቡት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሃይሉ እንደተናገሩት፤ የጤና ተቋማትና የህክምና አገልግሎት መስጫ መሳሪያዎች የሽብር ቡድኑ ዋነኛ የጥቃት ሰለባ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ተገቢ የህክምና አገልግሎት እንዳያገኝ ሆኗል ።

የጤና ተቋማት ተገቢዉን አገልግሎት እንዲሰጡ ለክልሉ የመልሶ ማቋቋም ጥረት ኢንስቲትዩቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ዛሬ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የተለያዩ ላቦራቶሪ እቃዎችና ተያያዥ የህክምና ግብአቶች ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ያሲን ሃቢብ በበኩላቸው በጦርነቱ ጉዳት ከደረሰባቸው የጤና ተቋማት መካከል አንድ ሆስፓታልና ከ21 በላይ የጤና ጣቢያዎች መልሰዉ ወደ አገልግሎት እንደገቡ ተናግረዋል።

ተቋማቱ መልሰው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የልማት አጋሮች ወሳኝ ሚና መጫወታቸውን ጠቁመዋል።

የሽብር ቡድኑ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ አንድ ሆስፒታል፣ በርካታ ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎችን መልሶ ወደስራ ለማስገባት ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ላደረገዉ ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም