በጦርነቱ ጉዳት ከደረሰባቸው ኢንዱስትሪዎች መካከል 65 የሚሆኑት በሙሉ አቅማቸው ማምረት ጀምረዋል

82

ሰኔ 10/2014/ኢዜአ/ በጦርነቱ ምክንያት ከተጎዱ 190 ኢንዱስትሪዎች መካከል 65 የሚሆኑት በሙሉ አቅማቸው ማምረት መጀመራቸውን ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።


ሚኒስቴሩ የአሥር ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።

ሪፖርቱን ያቀረቡት ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ የአሸባሪው የሕወሓት ቡድን በከፈተው ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ኢንዱስትሪዎችን ለመደገፍ  በጥናት ላይ የተመሰረተ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

በዚህም ከተጎዱ 190 አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ 65 የሚሆኑት በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ተደርጓል ብለዋል።

በተመሳሳይ 103 የሚሆኑት በከፊል ማምረት የጀመሩ ሲሆን 22 ኢንዱስትሪዎች ደግሞ ጉዳታቸው መጠን ከፍተኛ በመሆኑ ቶሎ ወደ ስራ ማስገባት አልተቻለም ብለዋል።

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር 'ኢትዮጵያ ታምርት' የሚል ንቅናቄ፣ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ክለሳ፣ የጸጥታ አካላትን የደንብ ልብስና ጫማ በአገር ውስጥ ምርት ማምረትን ጨምሮ አሥር ኢንሼቲቮችን ቀርጾ እየሰራ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

የጸጥታ አካላትን የደንብ ልብስና ጫማ በአገር ውስጥ ምርት ማምረትን በተመለከተ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሪን የማዳን፣ የገበያ ትስስርና የሥራ እድል ለመፍጠር ያለመ ነው።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የጸጥታ አካላት የደንብ ልብስ ከውጭ ለማስገባት የተደረጉ ስምምነቶች እንዲቋረጡ በማድረግ 29 አምራቾችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ትዕዛዝ አለ።

በተመሳሳይ የተማሪዎችን ጫማና ቦርሳም በአገር ውስጥ ለማምረት እየተሰራ ሲሆን እስካሁን 800 ሺህ 690 ጥንድ ጫማዎችን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በዙሪያዋ ለሚገኙ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ማቅረብ ተችሏል።

የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግም የምክር ቤት አባላት የአምራች ኢንዱስትሪውን የግብአት ችግር በዘላቂነት ከመፍታት፣ የጥሬ እቃና ኢንዱስትሪ ትስስርን ከማጠናከርና ሌሎች ጥያቄዎችን አንስተዋል።

ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል አምራች ኢንዱስትሪው እየገጠመው ካለው ችግር ውስጥ 55 በመቶ የሚሆነው ከግብአት አቅርቦት ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልዋል።

ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት አምራች ዘርፉ  በምጣኔ ሃብት እድገት ያለውን የመሪነት ሚና እንዲጫወት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ሚኒስትሩ በምላሻቸው ጠቅሰዋል።

በምክር ቤቱ የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር አማረች ባካሎ፤ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት እያደረገ ያለውን ተግባር በጥንካሬ አንስተዋል።

ሚኒስቴሩ የዘርፉን የግብአት፣ የፋይናንስ፣ የመሰረተ-ልማትና ሌሎች ችግሮችን የሚፈታ ስትራቴጂ በመቅረጽ ጠንካራ የኢንዱስትሪ ሥርዓት እንዲዘረጋ አሳስበዋል።

ከምክር ቤቱ የተሰጡ አስተያየቶችን በመውሰድ አምራች ኢንዱስትሪው በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት እንደሚሰሩ ኃላፊዎች ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ በትላንት መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

ምክር ቤቱ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን እንደገና ለማቋቋም በቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ላይ ጥያቄና አስተያየት በማንሳት በዝርዝር እንዲያይ ለቋሚ ኮሚቴው መርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም