ጅማ ዩኒቨርሲቲና ካማራ ኢጁኬሽን ኢትዮጵያ 5 መቶ ኮምፒውተሮችን ለ12 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ድጋፍ አደረጉ

194

ጅማ፣ሰኔ 9 2014 (ኢዜአ) ጅማ ዩኒቨርሲቲና ካማራ ኢጁኬሽን ኢትዮጵያ የተለያዩ የመማሪያ መጻህፍት የተጫነባቸው 5 መቶ ኮምፒውተሮችን ለ12 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ድጋፍ አደረጉ፡፡

ኮምፒውተሮቹ በርካታ የትምህርት መርጃ መጸሃፍት "በሶፍት ኮፒ "የተጫናባቸው በመሆኑ የዲጂታል ቤተመጻህፍትን ተደራሽ የሚያደርጉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በርክክብ ላይ የተገኙት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ጀማል አባ ፊጣ እንደገለጹት በጅማ ከተማ ፣በጅማ ዞን እና በቡኖ በደሌ ዞን ለሚገኙ 12 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ነው ድጋፉ የተሰጠው።

የትምህርት ጥራት ችግርን ለመቅረፍ የሚያግዙ በርካታ መጻህፍት በሶፍት ኮፒ የተጫነባቸው 5 መቶ ኮምፒዩተሮች ለትምህርት ቤቶቹ በድጋፍ መሰጠቱን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ለኮምፒውተሮቹ መደረጉን ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው 11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉንና ቀሪው ወጪ በካማራ ኢጁኬሽን ኢትዮጵያ የተሸፈነ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮምፒውተሮቹ "በኦፍ ላይን የፕላዝማ መማሪያ ሶፍትዌሮች፣ ዲጂታል ላይብረሪ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መለማመጃ ጥያቄና መልስ ያካተቱ መሆናቸውን ያነሱት ዶክተር ጀማል የትምህርት ቤቶቹ አመራሮች በአግባቡ በመያዝ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ አለባችው ነው ያሉት፡፡

ድጋፍ ከተደረገላቸው ትምህርት ቤቶች መካከል የሊሙ ገነት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አቶ ሪዳ ከማል  "ድጋፉ የመጻህፍት አቅርቦት ችግርን የሚፈታልን ሲሆን ተማሪዎች ተጨማሪ ማጣቀሻ መጸሃፍትን በማንበብ ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርግል" ብለዋል፡፡

በተለይም በኮምፒዩተሮች ላይ የተጫኑ የመማሪያ ሶፍትዌሮች የተሻለ ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ለማፍራት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

የበሻሻ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አቶ አብዱረህማን ናስር በበኩላቸው ለትምህርት ቤቱ 45 ኮምፒዩተሮች መሰጠቱን ገልጸው ድጋፉ ለተማሪዎች ውጤታማነት ጠቀሜታቸው የጎላ ነው ብለዋል።

በተለይም ተማሪዎች ለከፍተኛ ትምህርት ማለፊያ ፈተና መዘጋጀት የሚችሉበትን እድል የፈጠረ በመሆኑ የተገኘውን ሀብት ባግባቡ እንዲጠቀሙ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም