100 የልብ ህሙማን ህፃናት በህንድ ነፃ ህክምና ሊደረግላቸው ነው

179

ሰኔ 9/2014/ኢዜአ/ 100 የልብ ህሙማን ህጻናት በህንድ ነፃ ህክምና እንዲያገኙ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ።

የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከልና ሮተሪ ኢንተርናሽናል ስምምነቱን ተፈራርመዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ የልብ ህመም ያለባቸው ህፃናት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቅጽር ግቢ በሚገኘው የልብ ህክምና ማዕከል ህክምና እያገኙ ቢሆንም በግብአት አቅርቦት እጥረት የሚፈልገውን ያህል ህክምና መስጠት አለመቻሉን ገልጸዋል ።

በእነዚህና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች የልብ ህክምና ለማግኘት ተራ የሚጠባበቁ 7 ሺህ ህፃናት መኖራቸውን ተናግረዋል ።

በአራቱ ተቋማት መካከል የተደረገው ስምምነት 100 ህፃናት በህንድ ሀገር ህክምና እንዲያገኙ ከማስቻሉ በተጨማሪ የልብ ህሙማን ህክምና መስጫ ማዕከሉን በዘላቂነት ለመደገፍ  እንደሚያስችልም አብራርተዋል ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፤ አየር መንገዱ ከመደበኛ ተልዕኮው ባሻገር ማህበራዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።

በዚሀም አየር መንገዱ ወደ ህንድ ለህክምና ለሚሄዱት 100  ህፃናትና ለ100 አስታማሚዎቻቸው የሰጠው የደርሶ መልስ ነጻ የአየር ትኬት የዚሁ ማህበራዊ ሃላፊነቱ ማረጋገጫ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሮተሪ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ተሾመ ከበደ፤  የእናቶችና ህፃናት ጤና ጉዳዩ የሮተሪ ዋነኛ ዓላማ መሆኑን አስረድተዋል።

በስምምነቱ የህክምና እድሉን ያገኙት ህጻናት ቀዳሚ ተጠቃሚ ቢሆኑም አሁንም ወረፋ ከሚጠብቁት 7 ሺህ ህጻናት አንጻር ሲታይ ብዙ መስራት እንደሚገባ የሚያመላከት ነው ብለዋል።

በዚህ ሂደት ሮተሪ በህንድ ሀገር የሚከናወነውን የህጻናቱን የህክምና ሙሉ ወጪ እንደሚሸፍንና በቀጣይ የህክምና ማዕከሉን ለማገዝ የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሰላዲን ከሊፋ፤ ማዕከሉ በዓመት እስከ 1 ሺህ 500 የልብ ቀዶ ጥገና ለማድረግ የሚያስችል አቅም ቢኖረውም በአቅርቦት ችግር ከ500 ማለፍ እንዳልቻለ ገልጸዋል።

በህንድ ህክምናቸውን ተከታትለው የሚመለሱትን ህጻናት የጤና ሁኔታ ማዕከሉ በዘላቂነት እንደሚከታተልም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም