በጥቂት የዶሮ እርባታ ሥፍራዎች ሰሞኑን የተከሰተው የዶሮ በሽታ እንዳይዛመት ህብረተሰቡ አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ

300

ሰኔ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ እና ቢሾፍቱ ከተሞች ጥቂት የዶሮ እርባታ ሥፍራዎች ላይ ሰሞኑን የተከሰተው የዶሮ በሽታ እንዳይዛመት ህብረተሰቡ አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወስድ የግብርና ሚኒስቴር አሳሰበ።

የበሽታውን መንስኤና ምንነት ለማጥናት የጥናት ቡድን ተቋቁሞ ናሙና እየተሰባሰበ በመሆኑ ውጤቱ ሲታወቅ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል ተብሏል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባሳለፍነው ሳምንት በቢሾፍቱ እና በአዲስ አበባ ከተሞች ውስን የዶሮ እርባታ ቦታዎች የዶሮ በሽታ ተከስቷል።

በሽታው በንክኪ የሚዛመት በመሆኑ በእርባታ ቦታዎች በተወሰኑ ዶሮዎች ላይ ከተከሰተ ሌሎች ዶሮዎችን ሙሉ በሙሉ ስለሚያጠፋ ጥንቃቄ ያሻል ብለዋል።

በሽታው ከተከሰተ ጀምሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይስፋፋ በሽታውን መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በሚኒስቴሩ የተቋቋመው ግብረ-ኃይል በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢዎች ብቻ ተወስኖ እንዲቀር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሸታው እንዳይዛመት እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች መካከልም ዶሮ አርቢዎች ለተሻሻሉ የዶሮ ዝርያዎች እርባታ ከውጭ የሚገባውን የበሽታው መንስኤ እስኪጣራ የለማ እንቁላል ዝውውር መታገዱን ገልጸዋል።

የለማ እንቁላል ሲባል ለዶሮ እርባታ ከውጭ የሚገባ እንጂ ለሰው ምግብ ፍጆታ የሚውል እንዳልሆነ ገልጸዋል።

የተከሰተው በሽታ በቅጡ መቆጣጠርና መከላከል ካልተቻለ በአገር የዶሮ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት  የሚያስከትል በመሆኑ ዶሮ አርቢዎችና ሕብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

በዚህም በሽታውን የመከላከልና የመቆጣጠር እንዲሁም የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸው፤ አሁን ላይ ሥርጭቱና የሞት መጠኑ መቀነሱን ተናግረዋል።

የታመሙ ዶሮዎችን ወደ ገበያ የማውጣት አዝማሚያዎችን በግብረ-ኃይሉ በተሰራ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሻሻሎች እንዳሉ ገልጸው፤ አሁንም የበሽታው ምንነት እስኪታወቅ ጥንቃቄ እንዲደረግ መክረዋል።

በሽታው ባልተከሰተባቸው ቦታዎች ሌሎች ዶሮዎችን ባለማስገባት እና የራሳቸውንም ወደ ሌሎች ሥፍራዎች ባለማዘዋወር ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በዚህም በሽታው የተከሰተባቸው አርቢዎች ወደ ገበያ ባለማውጣትና የሞቱ ዶሮዎችንም በመቅበር እንዲሁም በሽታው የተከሰተባቸውን የእርባታ ጣቢያዎች ኬሚካል መርጨት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሕብረተሰቡን ከስጋት እና ሌሎች አርቢዎችን ከጉዳት እንዲሁም አካባቢን ከብክለት ለመታደግ የጋራ ትብብር ይፈልጋል ብለዋል።

በሽታው በሰው ጤና ላይ ያደረሰው ጉዳት እስካሁን ባይኖርም ሕብረተሰቡም በዶሮ እና በዶሮ ውጤቶች አጠቃቀም ላይ ጥንቃቄ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑንም  ተናግረዋል።

በሽታው እስካሁን በሰዎች ላይ ያደረሰው ጉዳት ባይኖርም ሚኒስቴሩ ሥራ ከመጀመሩ በፊት የተንቀሳቀሱ ዶሮዎች ስለሚኖሩም ለጊዜው የዶሮ እንቅስቃሴ መገደብ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ገልጸዋል።

በየእለቱ ያለውን ሁኔታ እና የጊዜ ገደቡ የሚነሳበትን ወቅት ለመወሰን የሚያጣራ ኮሚቴ መዋቀሩን ገልጸዋል።

በዶሮዎች ላይ የህመም ምልክት ካጋጠመ ዶሮ እና የዶሮ ውጤቶችን ለገበያ ባለማቅረብ ሊደርስ የሚችል ጉዳትን ለመቀነስ ማኅበረሰቡ ቀና ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም