የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ሳይንሳዊ ይዘቱን ጠብቆ ሀገር በቀል ዛፎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባው ተገለፀ

240

አዳማ ሰኔ 09/2014(ኢዜአ) ...በመጪው ሳምንት የሚጀመረው የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሳይንሳዊ ይዘቱን ጠብቆ ለምግብነትና ለደን ልማት የሚውሉ ሀገር በቀል ዛፎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባው የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለፁ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የዩኒቨርሲቲው ምሁራን መካከል የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ቦጃ መኮንን እንደገለፁት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ የአንድ ጊዜ ዘመቻ ብቻ መሆን የለበትም።

"በሀገራችን በህገ ወጥ ሰፈራ፣ በግጦሽና የእርሻ መስፋፋት ምክንያት የደን መመናመን በማጋጠሙ ለአፈር መሸርሸር፣ ድርቅ፣ የዝናብ መጠን ማነስ፣ ጎርፍና ለአየር ብክለት እየተጋለጠች ነው" ብለዋል።

እነዚህን የአካባቢ ጉዳት ለመከላከል፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የአየር ንብረት ተፅዕኖን ለመቋቋም የአረንጓዴ አሻራው የጎላ ፋይዳ አለው ሲሉም ገልፀዋል።

በዚህም ከመጪው ሳምንት ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው 4ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከዘመቻ ባለፈ ሳይንሳዊ ይዘቱን ጠብቆ መከናወን እንደሚገባው ነው ዶክተር ቦጃ ያሳሰቡት።

የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራሙ የደን ሀብቱንና የምናገኘው የዝናብ መጠን ከማሳደጉም ባለፈ የአፈር ለምነትን ለመጨመርና አሲዳማነትን ለመቀነስ ሚናው የጎላ በመሆኑ ከአንድ ወቅት ዘመቻ በመውጣት በክረምት መትከልና የተተከሉትን በበጋ መንከባከብ አለብን ነው ያሉት።

በተለይ ለችግኝ ተከላው የተዘጋጁ ጉድጓዶች ጥልቀቱና ስፋቱ ሳይንሳዊ ይዘታቸውን የጠበቁ መሆናቸው መረጋገጥ አለባቸው ያሉት ምክትል ፕሬዘዳንቱ፤ በዕለቱ ተቆፍሮ ወዲያውኑ መተከል የለባቸውም ብለዋል።

በተለይ ለደን ጥቅም የሚውሉ ሀገር በቀል ዛፎችና ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ዛፎች በዚህኛው የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ተለይተው ትኩረት ማግኘት አለባቸው ብለዋል።

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢው ጥበቃ መምህር ዶክተር ኬይረዲን አባ ተማም በበኩላቸው ሀገር በቀል ዛፎች እየተመናመኑና በውጭ የዛፍ ዝሪያዎች እየተዋጡ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

በተለይ የሀበሻ ፅድ፣ ኮሶ፣ ዝግባ፣ ዋንዛና ሌሎች በአሁኑ ወቅት እጅጉን እየተመናመኑ መሆናቸውን ገልጸው በአረንጓዴ አሻራው መርሃ ግብር ትኩረት ከተሰጣቸው ግን በቀላሉ እንደሚመለሱ ተናግረዋል።

የውጭ ዛፎች አብዛኛውን ጊዜ ከሀገራችን የአየር ጠባይ ጋር ስለማይስማሙ ይደርቃሉ፣ ያደጉትም ቢሆን አይቆዩም፣ በበሽታ የመጠቃት ሁኔታዎችም ስለሚታዩ ልዩ ትኩረት መስጠትና ማልማት እንደሚገባም ተናግረዋል።

አንዳንድ ቦታ ላይ የተተከሉ ችግኞች ተገቢው ክትትልና እንክብካቤ እየተደረገላቸው ባለመሆኑ "እየደረቁ ናቸው" ያሉት ዶክተር ኬይረዲን፤ በመሆኑም በሀገር ደረጃ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ህብረተሰቡ ዘላቂ ክትትልና እንክብካቤ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት ።

በተጨማሪም የሚተከሉ ችግኞች በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ የሚዘልቅ የክትትል፣ ቁጥጥርና ግምገማ አደረጃጀት መዘርጋት እንዳለበትም ተናግረዋል።

በዘንድሮው የ4ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ሁሉም ዜጎች ተፋሰሶችን መሰረት ባደረገ መልኩ በተከላው ወቅት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ የሃይል ማመንጫ ግድቦቻችን በደለል እንዳይሞሉ የድርሻችንን መወጣት አለብን ሲሉም ምሁራኑ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም