በክልሉ የህግ የበላይነትን በማስፈን የታራሚዎችን ሰብዓዊ መብቶች ለማስጠበቅ እየተሠራ ነው - ኮሚሽኑ

91

አሶሳ፤ ሰኔ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የህግ የበላይነትን የማስፈንና የህግ የታራሚዎችን ሰብዓዊ መብቶች ለማስጠበቅ እየሰራ መሆኑን የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጸጋዬ ተሰማ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በክልሉ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ የህግ ታራሚዎችን በሞያና በስነ-ምግባር  ለማነጽ ጥረት እየተደረገ ነው።

ታራሚዎቹን በማደራጀት በእደጥበብ፣ በእንስሳት እርባታና ሌሎችም የሙያ ዘርፎች የማስተማር ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም የቀለም ትምህርት እንዲያገኙ በማድግ የፍርድ ሂደታቸው ጨርሰው ከማህበረሰቡ ጋር ሲቀላቀሉ አምራችና ሠላማዊ ዜጋ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ኮሚሽነሩ የህግ ታራሚዎችን ሰብዓዊ መብቶች ለመጠበቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

"በቅርቡ ከአሶሳ ማረሚያ ቤት ያመለጡ አስር የህግ ታራሚዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል" ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡

"ታራሚዎቹ በየደረጃው በሚገኙ የጸጥታ አስከባሪዎች በቅንጅት ባደረጉት ክትትልና በህብረተሰቡ ትብብር በቁጥጥር ስር ውለዋል" ነው ያሉት፡፡

ታራሚዎች በፈጸሙት ከማረሚያ ቤት የማምለጥ ወንጀል ተጨማሪ ክስ ለመመስረት ፖሊስ ምርመራውን እያጠናቀቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም