በህገ ወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሬ ከሀገር ለማስወጣት የሞከረው ግለሰብ በአምስት ዓመት ፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ

3

አዳማ፣ ሰኔ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) በህገ ወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሬ ከሀገር ለማስወጣት ሲሞክር በአዳማ ከተማ በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰብ በአምስት ዓመት ፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ።

አሊ ኑሩ የተባለው ግለሰብ ከአዲስ አበባ ወደ ጂቡቲ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3/68918 ኢት በሆነ ከባድ የጭነት መኪና ውስጥ ከ168 ሺህ በላይ የአሜሪካን ዶላርና ዩሮ በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ለማሸሽ እየተጓዘ እያለ የካቲት 22 ቀን 2014 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወሳል።

May be an image of money

የከተማዋ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልሜቻ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ተከሳሹ የቀረበበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉና ድርጊቱን በማመኑ የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት በአምስት ዓመት ፅኑ እስራትና 10 ሺህ 500 ብር እንዲቀጣ ተወስኗል።

የተያዘው ገንዘብ ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን ፍርድቤቱ መወሰኑንም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በአዳማ ከተማ ገዳ ቀበሌ ከ20 ሺህ 600 በላይየሆነ ባለ 200 ሐሰተኛ የብር ኖት ይዞ የተገኘ ተጠርጣሪ ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልጸዋል።

May be an image of money

ግለሰቡ ትናንት ሰኔ 08 ቀን 2014 ዓ.ም በከተማዋ ፔንታጎን በተባለ ምሽት ቤት እየተዝናና ሳለ ከሌሊቱ በሰባት ሰዓት ጭለማን ተገን አድርጎ የተጠቀመበትን ሂሳብ ከፍሎ ለማምለጥ ሲል መያዙን ጠቅሰዋል።

ተጠርጣሪው በፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑንም አመልክተዋል።