በ10 ወራት ከአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ 418 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
በ10 ወራት ከአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ 418 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል

ሰኔ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) በ10 ወራት ከአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ 418 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛው ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ተካሄዷል።
ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን የ2014 በጀት አመት የ10 ወራት ሪፖርት ገምግሟል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ የተቋሙን የ10 ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

በሪፖርታቸውም በ10 ወራት ከአምራች ኢንዱስትሪው 498 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 418 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት የእቅዱን 84 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
የተገኘው ገቢ በ2013 በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 315 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር የ102 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ እንዳለውም ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው በጨርቃጨርቅና አልባሳት 153 ሚሊዮን ዶላር፣ በምግብና መጠጥ 93 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር፣ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች 33 ሚሊዮን ዶላር፣ በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብአቶች 22 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ዘርዝረዋል።
በማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂና ኢንጅነሪንግ ዘርፍም 16 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሲገኝ በስጋና ወተት ምርት ደግሞ 98 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል ብለዋል።