በአዲስ አበባ በተለያዩ ተቋማት ለከተማ ግብርና ልማት የሚውሉ ቦታዎች ተለይተዋል

238

አዲስ አበባ ሰኔ 09/2014(ኢዜአ) በአዲስ አበባ በተለያዩ ተቋማት ለከተማ ግብርና ልማት የሚውሉ ቦታዎች መለየታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ገለጸ።

በከተማ አስተዳደሩ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች የከተማ ግብርና ስራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

የጉብኝቱ አላማ ህብረተሰቡ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የከተማ ግብርና ስራዎችን ተሞክሮ በመውሰድ በቀጣይ በመኖሪያ አካባቢያቸው ይህንን ተሞክሮ እንዲያካፍሉ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽነር አቶ ባዩ ሽጉጤ፤ የጉብኝቱ ዓላማ በከተማ ግብርና የተጀመሩ ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማ ግብርና በተለይም በጓሮ አትክልቶች ላይ ማህበረሰቡ በስፋት እንዲሳተፍ ለማስቻል ጉብኝቱ ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የከተማ ግብርና ስራ በቤተሰብ ደረጃ ከሚሰሩ ስራዎች ባለፈ ትልልቅ ይዞታ ባላቸው የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትም በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በከተማ አስተዳደሩ ያሉ ትምህርት ቤቶች ትኩረት ሰጥተው እንዲሳተፉ መደረጉንም አክለዋል።

በጥቅሉ በመዲናዋ ከ3 ሺህ 200 በላይ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተለይተው ከእነዚህም 2 ሺህ 320 የሚሆኑት ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቁመዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ጠቁመው በሁሉም ክፍለ ከተሞች ለዚህ ስራ የሚውሉ የውሃ ማጠራቀሚያዎችን ለመግዛት የ71 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

እንዲሁም በሁሉም ክፍለ ከተሞች የውሃ ቦቴ ግዥ እንዲፈጸም የጨረታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አመልክተዋል።

የከተማ ግብርና ስራ እንደ ዘመቻ ለተወሰነ ወቅት ሳይሆን ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲመራ ኮሚሽኑ የጀመራቸው ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የጉብኝቱ ተሳታፊዎች በከተማዋ በአነስተኛ ቦታዎች ላይ እየተሰሩ ያሉ የከተማ ግብርና ስራዎች መደነቃቸውን ገልጸዋል።

የቀሰሙትን ተሞክሮ ወደ ተግባር ለመለወጥ እንደሚሰሩ ገልጸው ለምግብነት በጓሮ የሚለሙ አትክልቶች ለምግብ ዋሰትና መረጋገጥ የሚያግዙ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን የመዲናዋን የግብርና ምርት ፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣም፤ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የህብተሰብ ችግር ለመቅረፍ በከተማ አስተዳደሩ በአዋጅ ቁጥር 64/2011 የተመሰረተ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም