የፌደሬሽን ምክር ቤት ለከተማ ፕላን ረቂቅ አዋጅ ይሁንታን ሳይሰጥ ቀረ

73
አዲስ አበባ ሚያዚያ 22/2010 የፌደሬሽን ምክር ቤት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበለት የከተማ ፕላን ረቂቅ አዋጅ ይሁንታ ሳይሰጥ ቀረ። የፌደሬሽን ምክር ቤት 5ኛው የፓርላማ ዘመን ሦስተኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሄዷል። ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነት ላይ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ያለው አባተ የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል። አዋጁ እያደገ ከመጣው የከተሞች መስፋፋት ጋር አብሮ የሚሄድ ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ ፕላን እንዲኖር የሚያደርግ ነው ብለዋል። በተለይ አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበሰረብ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ በኩል አዋጁ ትልቅ  ፋይዳ አለው ነው ያሉት። የምክር ቤቱ አባላት በሰጡት አስተያየት አሁን ካለው የልማት ፍላጎት አኳያ አዋጁ ዘግይቷል የሚል ሀሳብ አንፀባርቀዋል። አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር የታቀደው እቅድ መልካም ቢሆንም ምን ያህል ሊሳካ ይችላል? የሚለው ከግምት ሊገባ ይገባል ብለዋል አባላቱ። ይሁን እንጂ እንደዚህ አይነት አሰራሮች ሲዘረጉ በቅድሚያ ህዝቡ ውስጥ ግልጽነት ሊፈጠር  ይገባል ብለዋል። ምክር ቤቱም በሚሰጠው ይሁንታ ላይ ዝርዝር ጉዳዮችን ማወቅ አለበት ፣ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ይሁንታ መስጠት ይከብዳል የሚል ሀሳብም አንስተዋል። የምክር ቤቱ አባል አቶ ተስፋዬ በልጅጌ እንደገለጹት፤ አዋጁ ምን ምን ጉዳዮችን ይዟል? የሚለውን በሚገባ ማወቅ እንዳለባቸው ገልጸው ይሄን ለማድረግ ደግሞ ጊዜ ይጠይቃል በቀጣይ ታይቶ መወሰን እንዳለበት ተናግረዋል። ሌላው የምክር ቤቱ አባል የሆኑት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው አዋጁ አገራዊ የፕላን ደረጃ እንዲኖር ከተፈለገ አዋጁ ግድ መሆኑን አብራርተው እንደ ቦታው ነባራዊ ሁኔታ መተገበር ግን የክልሎች ኃላፊነት መሆኑን አንስተዋል። በዚህ በኩል ከተሞች መተሳሰር አለባቸው ያሉት አቶ ገዱ ወጥ የሆነ አሰራር መኖሩ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል። አቶ ጋትሉዋክ ቱትም "አዋጁ አስፈላጊ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፤በአሁኑ ወቅት የጋምቤላ ክልል ከተሞች ያለፕላን በፍጥነት እየተስፋፉ ነው ስለዚህ አዋጁ በፍጥነት ይሁንታ ማግኘት አለበት" ብለዋል። ሌላዋ አባል ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ በበኩላቸው በአዋጁ ዙሪያ ህዝቡ መወያየትና ግልጽነት መፈጠር ነበረበት የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ ዶክተር አምባቸው መኮንን በሰጡት ምላሽ "ፕላን አይደለም የተዘጋጀው፤የተዘጋጀው ፕላኑ የሚመራበት አዋጅ ነው" ብለዋል። ስለ አዋጁ ግልጽነት ለመፍጠር በተለያዩ ክልሎች ለባለሙያዎች፣ባለድርሻ አካላትና አመራር አባላት ግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት መደረጉንም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። በተጨማሪም ከፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግና ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከተወጣጡ ባለሙያዎች ጋርም ውይይት መደረጉንም አንስተዋል። "ከተሞች በፍጥነት እየተስፋፉ ነው" ያሉት ዶክተር አምባቸው አዋጁ የሚዘጋጁ ፕላኖች ዘመናዊነት እንዲላበሱ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይ አዋጁ በማዕከላዊነት በፌደራል ብቻ የሚተገበር ሳይሆን ክልሎችን የሚያሳትፍ ማዕቀፍ ነው ብለዋል። ምክር ቤቱ በአዋጁ አስፈላጊነት ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ በ 30 ድጋፍ በ 60 ተቃውሞና በ1 ድምጸ ተአቅቦ ለሌላ ጊዜ እንዲታይ ወስኗል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም