ለማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን በመደገፍ በኩል የህብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

272

ሶዶ ፤ሰኔ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ።

የመጀመሪያው የደቡብ ክልል የማህበራዊ ጥበቃ ኮንፍረንስ በወላይታ ሶዶ እየተካሄደ ነው።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ በኮንፍረንሱ ላይ እንዳሉት ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ለመደገፍና ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ ርብርብ ሊደረግ ይገባል።

መንግስት ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ለመደገፍና ለማቋቋም እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላትን ያሳተፈ ብሔራዊ የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ቀርፆ በመተግበር ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

መንግስት ለማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ለመደገፍ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትን የሚያመጡ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የማህበራዊ ጥበቃ ሽፋንና ተደራሽነት በየጊዜው ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፤ ዜጎች አሁንም ለተለያዩ ችግሮች ሲዳረጉ እንደሚስተዋል ገልጸዋል።

በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለማቃለል የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት ግንባታን ለማጠናከር ትኩረት እንዲደረግ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠይቀዋል።

የማህበራዊ ጥበቃ ሽፋን በማሳደግ የዜጎችን ተጋላጭነት ለመቀነስና ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

የደቡብ ክልል የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኦንጋዬ ኦዳ በበኩላቸው ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ለመደገፍ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት ይገባል ብለዋል።

የዜጎችን ማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭነት ለመከላከልና ደህንነታቸውን ለመጠበቅ የተለያዩ ስልጠናዎችና የስነ-ልቡና ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግስትና ባለድርሻ አካላት ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት እያደረጉት ያለው ስራ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱንም አመልክተው፤ችግሩን ከመነሻው ለመቀነስ የባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ለአብነትም ሴፍቲኔትን የማስፋፋት፣ ማህበራዊ አገልግሎት ትስስርን የማሳደግ እንዲሁም የስራ እድሎችን የማስፋፋት ተግባራትን ጠቅሰዋል።

ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች አምራች እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል።

ማህበራዊ ጥበቃ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍ፣ማቋቋምና ከሚደርስባቸው ችግሮች መከላከል ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው በክልል ደረጃ የሚካሄደው ኮንፍረንስ በምሁራን ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው የወጣው መርሃ ግብር ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም