በኢትዮጵያ ጽንፈኝነት በተለያዩ አውዶች የሚገለጽ አደገኛ አካሄድ በመሆኑ ያለ ልዩነት ልንታገለው ይገባል

191

ሰኔ 9 ቀን 2014 (ኢዜአ ) በኢትዮጵያ ጽንፈኝነት በተለያዩ አውዶች የሚገለጽ አደገኛ አካሄድ በመሆኑ ያለ ልዩነት ሁሉም በጋራ ሊታገለው እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚዘጋጀው አዲስ ወግ የውይይት መድረክ "ከጽንፈኞች መሐል ወርቃማውን አማካይ ፍለጋ" በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት የማህበራዊ ስነ-ልቦና ምሁሩ ፕሮፌሰር ሃብታሙ ወንድሙ፤ጽንፈኝነት አፍሪካን እየተፈታተነ ያለ ስጋት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያም የጽንፈኝነት አካሄድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው ያልተገራ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ደግሞ ችግሩን ይበልጥ እያባባሰው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም በኢትዮጵያ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2019 በማህበራዊ ሚዲያ ከተሰራጩ መረጃዎች መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት የሃይማኖትና የብሔር ይዘት ያላቸው መሆኑ በጥናት መረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡

አብዛኛዎቹ መረጃዎች ደግሞ በውስጣቸው ጽንፈኝነትን የሚያመላክቱ የጥላቻ ንግግሮች መሆናቸውን ነው ያብራሩት፡፡

ጽንፈኝነት በአንድ ጊዜ ሳይሆን በሂደት የሚገነባ መገለጫ መሆኑን የሚናገሩት ፕሮፌሰር ሃብታሙ፤ከዚህ አኳያ የመከላከሉ ስራም ከታችኛው የህብረተሰብ መዋቅር ጀምሮ በሂደት መገንባት እንዳለበት አንስተዋል፡፡

በተለይ ከቤተሰብ ጀምሮ ልዩነትን የሚቀበል የዲሞክራሲ ባህልን ማጎልበት ይገባል ነው ያሉት፡፡የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ጽንፈኝነት "የኔ ብቻ ትክክል፤ እኔን ብቻ መቀበል አለባችሁ" በሚል አመለካከት እንደሚገለጽ ይናገራሉ፡፡

በዚህም ጽንፈኝነት በሁሉም ቦታ በተለያዩ አውዶች የሚገለጽ አደገኛ አካሄድ በመሆኑ ያለ ልዩነት በጋራ ልናወግዘውና ልንታገለው ይገባል ነው ያሉት፡፡

ጽንፈኝነትን የመታገሉ ስራ የራስን ባህሪና አመለካከት ከመግራት እንደሚጀምር ጠቅሰው፤በተለይ የሃይማኖት አባቶች በአስተምሯቸው የራሳቸውን አስተሳሰብ ሳይሆን ትክክለኛውን የሃይማኖት እሴት ማስተላለፍ እንዳለባቸው ጠይቀዋል፡፡

ደካማ የመንግስት መዋቅር ለጽንፈኝነት አካሄድ መስፋፋት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የገለጹት ተሳታፊዎቹ፤ ከዚህ አኳያ በተለይ የመንግስት የጸጥታ መዋቅሮች ተናበውና ተጠናክረው ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትም ማህበረሰቡን የሚያቀራርቡ ገንቢ ተግባቦቶች ላይ ትኩረት በማድረግ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ጽንፈኝነትና የጥላቻ ንግግሮችን መመከት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

መገናኛ ብዙሃን የማህበረሰብ መወያያ መድረክ ሊሆኑ እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡መድረኩ ከሰዓት በኋላም ''የጽንፈኝነት ስነ-ልቦናዊ መነሻ፣መገለጫዎችና አስከፊነት'' በሚሉ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የሚካሄድ ሲሆን በነገው እለትም መድረኩ ይቀጥላል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም