መንግስት የጀመረው ህግ የማስከበር ስራ ሰላምን እያረጋገጠ በመሆኑ የሚጠበቅብንን እንወጣለን

ሀረር ፣ ሰኔ 09 /2014 (ኢዜአ) መንግስት የጀመረው የህግ ማስከበር እርምጃ የሀገርን ሰላም እያረጋገጠ በመሆኑ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሀረር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ማብራሪያ በበርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ግልጸኝነት የፈጠረላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ የተጀመረው የህግ ማስከበር ስራ ተገቢና ሁሉም ሊደግፈው የሚገባ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ብዙነሽ ጌታቸው እንዳሉት ማብራሪያው የህግ ማስከበር እርምጃው ህገወጦች በህዝቡ ላይ የሚያደርሱትን ችግር በማስቀረት ሰላምን እያመጣ መሆኑን የተረዱበት ነው።

ከመንግስት ጎን በመቆም የህግ ማስከበር አላማው ፈጥኖ እንዲሳካ የህዝብንና የሀገር ሰላምን የሚያውኩ ህገወጦችን ለህግ እንዲቀርቡ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

በጋዜጠኝነት ሞያ ውስጥ ተሸሽገው ህዝብን ለማጋጨት የተሳሳቱ መረጃዎችን በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የሚያሰራጩ ግለሰቦች መበራከታቸውን የሚናገሩት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ሚልዮን ጥላሁን ናቸው።

ከሞያው ስነ-ምግባር ውጭ የሀገርን ሰላም በማደናቀፍና ህዝብን ለመከፋፈል የሚከናወኑ ተግባራትን ለመቆጣጠር እየተወሰደ ያለው የህግ የበላይነት ማረጋገጥ ተግባር ላይ በቂ መረጃ ከማብራሪያው ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

ጋዜጠኞች ለህግ ተገዢ በመሆን ህዝብንና ሀገርን የሚጠቅሙ ተግባራትን ሊሰሩ ይገባል ሲሉም ጠቅሰዋል።

ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመሆን አጥፊዎችን ለህግ ማቅረብ ይገባዋል ያሉት የከተማው ነዋሪ አቶ አበባው ነጋ ናቸው፡፡

መንግስትም በአጥፊዎች ላይ መውሰድ የጀመረውን ህጋዊ እርምጃ በመደገፍ አጥፊዎችን ለህግ አሳልፈን መስጠት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም