በዞኖቹ ከ636 ሚሊየን በላይ የተለያዩ ችግኞችን የመትከል ስራ እየተከናወነ ይገኛል

1

ሰኔ 9 ቀን 2014 (ኢዜአ)በምዕራብ ሸዋና በባሌ ዞኖች እንዲሁም በነቀምቴ ከተማ አስተዳደር በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ636 ሚሊየን በላይ የተለያዩ ችግኞች ዝግጅትና የመትከል ስራ እየተከናወነ መሆኑን የየዞኖቹና ከተማ አስተዳደሩ የግብርና ጽህፈት ቤቶች አስታወቁ።

እየተተከሉ ከሚገኙ ችግኞች መካከል ከ40 ሚሊየን በላይ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው እንደሆኑም ተመልክቷል።

በምዕራብ ሸዋ ዞን 22ቱም ወረዳዎች ከ207 ሚሊዮን በላይ ጉድጓድ መቆፈሩንና የችግኝ ማፍላት ዝግጅት ስራው መቀጠሉን የገለጹት ግብርና ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ሀብት፣ የተፋሰስና የደን እንክብካቤ ቡድን መሪ አቶ ገዛኸኝ ቅናጢ ናቸው።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለመትከል ከታቀደው 392 ሚሊዮን ችግኝ በተጨማሪ ለምግብነት የሚውሉ 39 ሚሊየን የፍራፍሬ ችግኞችም በዞኑ ለተከላ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡

ችግኞቹ የሚተከሉት በ106 ሺህ 544 ሄክታር መሬት ላይ መሆኑንም አቶ ገዛኸኝ አመልክተዋል።

የዞኑ ነዋሪዎች በበኩላቸው በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የተዘጋጁ የዛፍ ችግኞችን ለመትከል ጉድጓዶቹን በዘመቻ እያዘጋጁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በአምቦ ወረዳ የሜጢ ቀበሌ አርሶ አደር ሚሬሳ ገለታ በሰጡት አስተያየት ችግኝ መትከል ህይወትን ማስቀጠል በመሆኑ የተከሉትን ችግኝ ተንከባክበው እንዲፀድቅ ተግተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮ ዓመት ለእንስሳት መኖና ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞችንም በስፋት ለመትከል አስፈላጊውን ዝግጅት እንዳደረጉ ጠቁመዋል።

ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቡልቶ ፉፋ በተያዘው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የአፈር ለምነት የሚጨምሩና ለከብቶች መኖ የሚያገለግሉ የተለያዩ ዝሪያ ያላቸውን ችግኞች በመትከል ድርቅን ለመከላከል እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ በባሌ ዞን በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 243 ሚሊዮን የተለያዩ አይነት ችግኞችን ለመትከል የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡

ከዚህ መካከል ከ12 ሚሊዮን የሚበልጡ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የቡና፣ አፕል፣ አቮካዶና ሌሎች የአርሶ አደሩን ኑሮ ለመቀየር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው የቆላና የደጋ ፍራፍሬዎች መሆናቸውን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አልይ መሀመድ ገልጸዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት በዞኑ እስከ አሁን ከተተከሉት ችግኞች መካከል 11 ሚሊዮን የሚሆኑት ከምርምር ማዕከላት የወጡና የተሻሻሉ ዝሪያ ያላቸው የቡና ችግኞች ይገኙበታል፡፡

የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ የሀረና ቡሉቅ ወረዳ ነዋሪ አቶ ሀሰን መህሙድ በሰጡት አስተያየት በቡና ልማት የቆየ ልምድ ቢኖራቸውም ምርጥ ዘር ስለማይጠቀሙ የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ እንደልነበሩ አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከምርምር ማዕከላት ተለቀው ከአካባቢያቸው ጋር የተላመዱ የቡና ምርጥ ዘር በመትከል እየተንከባከቡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በዘንድሮ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ የአቮካዶና ማንጎ ተክል ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የልማቱ ተሳታፊ ሱልጣን ኡስማን ናቸው፡፡

“ለችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ስኬት ከመንግስት ድጋፍ በተጓዳኝ የፍራንክፈርት ድርጅት በችግኝ አቅርቦቱ ላይ ያደረገልን ድጋፍ ከፍተኛ በመሆኑ እናመሰግነለን” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በነቀምቴ ከተማ አስተዳደርም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚበልጥ ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱን የገለጹት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ የግብርና ክላስተር ጽህፈት ቤት ነው፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አሰፋ እንዳስታወቁት በከተማ አስተዳደሩ በተያዘው ክረምት የሚተከል 1 ሚሊዮን 226 ሺህ 35 የተለያዩ ዓይነት ችግኞች ተዘጋጅተዋል።

ችግኞቹ የተዘጋጁት በ60 የመንግሥትና የግል የችግኝ ጣቢያዎች ሲሆን በተጨማሪም በአንድ ጀምበር ብቻ ከ882 ሺህ በላይ የተለያዩ ችግኞችን በ15 ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

ለምግብነት ከሚውሉ ችግኞች መካከል ከ196 ሺህ የሚበልጥ የአቮካዶ ችግኝ መሆኑንም ሃላፊው አመልክተዋል።

ከመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች መካከል የከተማው 03 ቀበሌ ነዋሪና ጡረተኛ አቶ በቀለ ፉፋ በሰጡት አስተያየት ጡረታ ከወጡ በኋላ ስራ ሳይፈቱ በመኖሪያ ቤታቸው አካባቢ የአቮካዶ ችግኝ እያዘጋጁ ይገኛሉ፡፡

ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ አቮካዶ በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውንና በዚህ ዓመትም 6 ሺህ 570 ምርጥ የአቮካዶ ችግኝ ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የከተማው 07 ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ደረጀ ጥላሁን በበኩሉ ኤቢሴ፣ መገርሳ እና ገመቹ ኃ.የተ.የግ.ማህበር በሚል ተደራጅተው ከ190 በላይ የተለያዩ ችግኞችን በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

ዘንድሮ ከአቮካዶና ሌሎች 15 ሺህ የተለያዩ ችግኞች ሽያጭ 130 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን የተናገሩት ወጣት ደረጀ፤ የገበያ ትስስር ከተፈጠረላቸው በዚህ ዓመት ከተለያዩ ችግኞች 12 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅደው እየሰሩ መሆኑን አስታውቋል፡፡