በምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የልማት ትስስሩን ለማጠናከር የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል

1

ሰኔ 9 ቀን 2014 (ኢዜአ)በምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የልማት ትስስሩን ለማጠናከር የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ፍስሐ ሻውል ገለጹ።

የአፍሪካ ቀንድ የሦስት አህጉራት ማለትም የአፍሪካ፣የእስያና አውሮፓ መገናኛ መሆኑ የፖለቲካ ፍላጎት የስህበት ማዕከል አድርጓታል።

በዓለም የኢኮኖሚና የንግድ እንዲሁም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ቁልፍ ጂኦ- ፖለቲካዊ ሚና እንዳለውም ይታመናል።

በቀጣናው እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ቢኖርም በየጊዜው የሚስተዋለው የሰላም እጦት የአካባቢውን ሀገራት በሚጠበቀው ልክ የልማት ውጤት እንዳያስመዘግቡ አድርጓቸዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ፍስሐ ሻውል በተለይም ለኢዜአ እንደገለጹት፤በምስራቅ አፍሪካ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በጋራ በማልማት ተጠቃሚ ለመሆን መሥራት ይገባል ብለዋል።

በቀጣናው ዘላቂ የልማት ትስስር ለመፍጠር ደግሞ የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ፣ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳንና ጂቡቲን በማስተሳሰር ቀጣናውን ለማሻገር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሰላምና ጸጥታ ጉዳይም አብሮ የሚታይ ዋነኛ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለቀጣናው የልማት ትስስርና የጋራ ተጠቃሚነት እየሰራች መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ፍሰሐ፤ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚነት ወሳኝ መሆኑን ጠቅስዋል።

በቀጣናው ተስፋ ሰጪና ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት ሽግግር እየታየ መሆኑን ጠቅሰው፤በቅርቡ ሶማሊያ ያካሄደችው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ጥሩ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በብዙ መስኮች በትብብር እየሰሩ በመሆኑ በቀጣይም በወደብ አጠቃቀምና ሌሎችም የትብብር መስኮች አብረው ይሰራሉ ብለዋል።

የንግድ ልውውጥን ለማሳደግና የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን ለማድረግ በጋራ እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።

በቅርቡ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ የምትገኘው ኬንያም በጥሩ አካሄድ ላይ መሆኗን ጠቅሰው፤ የሁለቱ አገሮች የሰላም፣ ልማትና ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በደቡብ ሱዳን ልዩነቶችን በሰላም በመፍታት የሁለቱ ኃይሎች ጥምር መንግሥት ውጤታማ እንዲሆን የኢትዮጵያ ድጋፍ እንደማይለይ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያንና ጎረቤት ሀገራትን በሜጋ ፕሮጀክቶች፣በመንገድ መሰረተ-ልማት፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝምና ሌሎችም መስኮች ለማስተሳሰር የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውንም አምባሳደር ፍስሐ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የፍጥነት መንገድ መሰረተ-ልማቶችና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችም አካባቢውንና መላው አፍሪካን ለማስተሳሰር ታቅደው እየተተገበሩ መሆኑን ገልጸዋል።