መንግስት የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር በሚያደርገው ሁሉን አቀፍ ጥረት የበኩላችንን እንወጣለን- የሠመራ-ሎግያ ከተማ ነዋሪዎች

82

ሰኔ 9 ቀን 2014 (ኢዜአ)መንግስት የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር በሚያደርገው ሁሉን አቀፍ ጥረት የበኩላቸዉን እንደሚወጡ የሠመራ-ሎግያ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የሰመራ-ሎግያ ከተማ ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የሰጡት ማብራሪያ መንግስት በተለያዩ ዘርፎች እያከናወነ ባለው እንቅስቃሴ ግልጸኝነትን የፈጠረ ነው ብለዋል።

ከሎግያ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ አቦ አወል  ''ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ ማብራሪያ ሀገራችን በውስጥ ችግሮችና አለም አቀፍ ጫናዎች እየተፈተነች ቢሆንም በብዙ መመዘኛዎች እድገቶች መኖራቸው ተስፍ ሰጪ ነው'' ብለዋል።

የታዩ ጅምር ተስፋዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሀገርን ወደ ትርምስ ለማስገባት አፍራሽ ተልዕኮ ወስደው እየተንቀሳቀሱ በነበሩ አካላት ላይ እየተወሰደ ያለው ርምጃ የሀገርና የህዝብን ሰላም ያረጋገጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ አዳጋች እያደረገ የሚገኘውን የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር እየተወሰደ ያለው ርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀው፤ ለስኬታማነቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የሰመራ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሰዲቅ በድሩ በበኩሉ በግብርና ፣በወጪ ንግድና መሠረተ-ልማት ሴክተሮች አበረታች ውጤት መታየቱን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ መረዳት መቻሉን ተናግል።

የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት መንግስት የአጭርና ረጂም ጊዜ እቅዶችን ነድፎ አየሰራ መሆኑ የሚደገፍ ነው ብል።

ችግሩ ጊዜ የማይሰጥ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ የመንግስትን ትኩረት ይሻል ያለው ወጣት ሰዲቅ፤የመንግስትን ጥረት በሚችለው አቅም ሁሉ እንደሚያግዝ አስረድቷል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ህብረተሰቡ በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ግራ ይጋባባቸው የነበሩ የተሳሳቱ መረጃዎችን ያጠራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሰመራ ከተማ ነዋሪው አቶ አሊ መሀመድ ናቸው።

ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እያሻቀ የሚገኘው የኑሮ ውድነት ፈተና መሆኑን አመልክተው፤ በተለይም የመሰረታዊ ፍጆታ አቃዎችን የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት በመንግስት የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

በዘርፉ የሚታየውን ህገ ወጥነት በማጋለጥና በመከላከል ረገድ ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻቸውን እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል።

ሌላው የሎግያ ከተማ ነዋሪ ሼክ ኡስማን ዳውድ በበኩላቸው መንግስት የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥና ሀገራዊ ልማቱንም ለማስቀጠል ያደረገው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል።

የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት አበረታች ጅምሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

የኑሮ ውድነቱ በውስብስብ ችግሮች የተተበተበ መሆኑን አመልክተው፤ ያልተገባ ጥቅም ለማካበት የሚንቀሳቀሱ  ነጋዴዎችና ተባባሪ የሆኑ የመንግስት አካላትን በማጋለጥ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም